አስተርአየ ዘኢያስተርኢ — የማይታየው ታየ

«አስተርአየ ዘኢያስተርኢ — የማይታየው ታየ»

(ድጓ ዘዘመነ አስተርእዮ)

መግቢያ

ዘኅቡእ እምኅቡኣን ወልዑል እምልዑላን ከተሠወሩት የተሠወረ፥ ከልዑላን በላይ ልዑለ ባሕርይ የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር ዓለምን ከመፍጠሩ አስቀድሞ ባሕርዩን በባሕርዩ ሠውሮ የኖረ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ። ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስም ይህን ሲያስረዳ፦ «ወአስተርአየ በደኃሪ መዋዕል በእንቲኣነ — በኋለኛው ዘመን ስለእኛ ተገለጠ» በማለት። ቅድመ ዓለም ባሕርዩን በባሕርዩ ሠውሮ ይኖር የነበረ ስለእኛ (እኛን ለማዳን) የተገለጠ መሆኑን አስረድቷል። (1ጴጥ. 1፥20)

የማይታየው ፈጣሪ ዓለምን በመፍጠሩ ተገልጿል። ዓለምን ከፈጠረበት ጀምሮ በተለያየ ጊዜ በልዩ ልዩ ምሳሌ በፍጹም ሃይማኖት፥ በምስጋና፥ በጸሎት፥ በትሕትና፥ በንጽሕና፥ በቅድስና ሁነው ለሚሹትና ለሚፈልጉት ሁሉ በየጊዜው ተገልጿል።

በየጊዜው ሲገለጽም በራእይ፥ በሕልም፥ በአምሳል፥ በረድኤት በመሳሰለው ለወዳጆቹ የተገለጸላቸው ሲሆን፤ በኩነት የተገለጸው ግን በዘመነ ሥጋዌ ነው። ይህም በቅደም ተከተል እንደሚከተለው በዚህ ጽሑፍ በመጠኑ ተዳሷል። በመሆኑም፦

  1. ዘመነ አስተርእዮ ምን ማለት ነው?
  2. አስተርእዮ በጥንተ ፍጥረት
  3. አስተርእዮ በማኅበረ መላእክት
  4. አስተርእዮ በዘመነ አበው
  5. አስተርእዮ በዘመነ መሳፍንት
  6. አስተርእዮ በዘመነ ነገሥት
  7. አስተርእዮ በትንቢተ ነቢያት
  8. አስተርእዮ በዘመነ ሥጋዌ
  9. አስተርእዮ በባሕረ ዮርዳኖስ
  10. ማጠቃለያ፥ በሚሉ ንኡሳን አርእስት በቅደም ተከተል በአጭሩ ይቀርባል።

 

1) ዘመነ አስተርእዮ ምን ማለት ነው?

«ዘመነ አስተርእዮ» የሚለው ሐረግ ከሁለት የግእዝ ቃላት የተገኘ ሲሆን፤ «ዘመን» ማለት በቁሙ ዘመን፥ ዓመት፥ ሴኮንዶች ደቂቃዎችን፥ ደቂቃዎች  ሰዓታትን፤ ሰዓታት ዕለታትን፥ ዕለታት ሳምንታትን፥ ሰምንታት ወራትን፥ ወራት ዘመንን ያስገኛሉ። አንዱ ዘመን ዘመነ መፀው፥ ዘመነ ሐጋይ፥ ዘመነ ጸደይ ዘመነ ክረምት ተብሎ በ4ት ተከፍሏል። ከአንዱ ዘመን ውስጥም ዘመነ ጽጌ፥ ዘመነ አስተምህሮ፥ ዘመነ ስብከት፥ ዘመነ ልደት፥ ዘመነ አስተርእዮ፥ … ወዘተ. እየተባለ ተሰይሟል። ስለዚህ «ዘመን» የሚለውን ቃል የግእዝ መዝገበ ቃላት በቁሙ ዘመን፥ ዓመት፥ ጊዜ፥ ወራት በየስሙና በየክፍሉ ብሎ ተርጒሞታል። (መጽ.ሰዋ.ወግስ ገጽ 4)@3)

«አስተርእዮ» ማለት ደግሞ መታየት፥ መገለጥ ማለት ነው። ሁለቱ ቃላት ሲናበቡ «ዘመነ አስተርእዮ» የሚለውን ሐረግ ይሰጡናል፤ ዘመነ አስተርእዮ የሚለው ሐረግም ሲተረጐም የመታየት ዘመን፥ የመገለጥ ጊዜ … ተብሎ ይተረጐማል። በሌላ ቃልም «ኤጲፋንያ» ወይም በጽርዕ «ሄፒፋንያ» የሚለውን ቃል በተመሳሳይ ትርጓሜ አስተርእዮ መታየት፥ መገለጥ፥ ዕለተ ጥምቀት በማለት ይተረጒመዋል። (መጽ.ሰዋ.ወግስ ገጽ 2)%)

ቅዱሳን ሐዋርያትም በመጽሐፈ ዲድስቅልያ «ግበሩ በዓለ ኤጲፋንያ ዘውእቱ በዓለ ጥምቀት፥ ወይኩን በኀቤክሙ ክቡረ፥ እስመ ቦቱ ወጠነ እግዚእነ ከመ ያረኢ ስብሐተ መለኮቱ አመ ተጠምቀ በውስተ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ — የኤጲፋንያ (የአስተርእዮ) በዓልን አድርጉ፥ እርሱም በዓለ ጥምቀት ነው፤ በእናንተም ዘንድ የከበረ ይሁን። ጌታችን በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ በተጠመቀ ጊዜ የጌትነቱን ክብር ያሳይ ዘንድ ጀምሮበታልና» ሲሉ፥ የበዓሉን ታላቅነት ገልጸው ትእዛዝ አስተላልፈዋል። (ዲድስቅልያ አንቀጽ @9)

ስለዚህ ጌታ በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ፥ አብ በደመና ላይ «የምወደው ልጄ ይህ ነው» ብሎ ሲመሰክርለት፥ መንፈስ ቅዱስም በራሱ ላይ በአምሳለ ርግብ ወርዶ ሲቀመጥ ምሥጢረ ሥላሴ የተገለጠበት ስለሆነ ዘመነ አስተርእዮ ተብሏል።

በመሆኑም ከዚህ አስቀድሞ ለወዳጆቹ በየጊዜው እንዴት ይገለጽላቸው እንደነበር በመጠኑ መግለጽ አስፈላጊ ይሆናል።

 

2) አስተርእዮ በጥንተ ፍጥረት

ዓለምን ከመፍጠሩ አስቀድሞ የማይታይ የማይመረመር የነበረው ጌታ ዓለምን በመፍጠሩ ፈጣሪነቱ፥ ህልውናው፥ አምላክነቱ፥ ጌትነቱና ክብሩ በፍጥረቱ ለፍጥረቱ ታውቋል። ይህንንም ብርሃና ለቤተ ክርስቲያን የተባለው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲመሰክር «ወዘኢያስተርኢ እግዚአብሔር እምፍጥረተ ዓለም ይትዐወቅ በፍጥረቱ በሐልዮ ወበአእምሮ ወከመዝ ይትአመር ኀይሉ ወመለኮቱ ዘለዓለም — ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ታይቶ የማይታወቅ እግዚአብሔር የፈጠረውን ፍጥረት በማሰብና በመመርመር ይታወቃል፤ ከሃሊነቱ፥ የዘለዓለም ጌትነቱም እንዲህ ይታወቃል» ብሏል። (ሮሜ 1፥@፤ መዝ. 08፥1)

ስለዚህ «ሥነ ፍጥረት» የመጀመሪያው የእግዚአብሔር መገለጥ መሆኑን በዚህ እንገነዘባለን።

 

3. አስተርእዮ በዓለመ መላእክት

የሥነ ፍጥረትን ምሥጢር አምልቶ አስፍቶ የጻፈው ኤጲፋንዮስ የተባለው የቤተ ክርስቲያን ሊቅ አክሲማሮስ በተባለው መጽሐፉ እንደገለጸው፥ ጌታ በመጀመሪያ ከፈጠራቸው ፍጥረታት ለባውያን ነባብያን ሁነው የተፈጠሩ ቅዱሳን መላእክት ናቸው። ጌታ እነርሱን ፈጥሮ ተሰውሯቸዋል።

ትጉሃን መላእክትም በአእምሮ በለብዎ ተፈጥረዋልና፥ ማን ፈጠረን? ከወዴትስ መጣን? እያሉ ሲመራመሩ፥ አቡሃ ለሐሰት የተባለው ሐሰተኛው መልአክ ድምፃቸውን ሰምቶ ወደላይ ቢያዳምጥ የሚሰማው ድምፅ ቢያንጋጥጥም የሚያየው ገጽ ስለአጣ እኔ ፈጠርኳችሁ … በማለት ለማሳሳት ሲሞክር መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል «አምላካችንን እስከምናገኘው ድረስ በያለንበት እንቁም (እንጽና)» ብሎ አጽንቷቸዋል። በዚህ ጊዜ አምላከ ብርሃን እውነተኛው የብርሃን ጌታ እግዚአብሔር በብርሃን ተገልጾላቸዋል። «ወውእቱ ብርሃነ ኮኖሙ ጥበበ ወአእምሮ እንዳለው ሊቁ … በዚህ ብርሃን አንድነቱን ሦስትነቱን ገልጾላቸው ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር … ብለው አመስግነውታል። (መቅ.ወን. አክሲማሮስ፥ ሥነ ፍጥረት)

 

4. አስተርእዮ በዘመነ አበው

ጌታ በዘመነ አበው በየዘመኑ ለአባቶቻችን በልዩ ልዩ ራእይ ተገልጿል። ይኸውም በገሃድ፥ በራእይ በሕልም በልዩ ልዩ አምሳል መገለጹን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ። ለማስረጃም፦

  • ለአባታችን ለአዳም በበደለ ጊዜ ለዘለፋ፥ ንስሓ በገባ ጊዜ ለውሂበ ተስፋ መገለጹ፥ (ዘፍ. 3፥9፤ መጽሐፈ ቀሌምንጦስ)
  • ለአቤል መሥዋዕት ባቀረበ ጊዜ መገለጹ (ዘፍ. 4፥4)፥ ለሄኖክ ወደ ደቂቀ ሴት በላከው ጊዜ መገለጹ፥ (ሄኖ. 4፥$9)
  • ለኖኅ ቅድመ ማየ አይኅ መርከብ እንዲሠራ ባዘዘው ጊዜ፥ ድኅረ ማየ አይኅ ኖኅ መሥዋዕት ባቀረበ ጊዜ መገለጹ፥ (ዘፍ. 6፥03፤ 7፥1፥ 8፥@1፥ 9፥1፥ @2፥04)
  • ለአብርሃም በተደጋጋሚ መገለጹ፤ ይልቁንም በአምሳለ እንግዳ በቤቱ (በድንኳን) ማረፉ፥ (ዘፍ. 02፥1፤ 7፤ 05፥1፤ 08፥#3)
  • ለይስሐቅ መገለጹ፥ (ዘፍ. @6፥@4፤ ለያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ መገለጹ በመጽሐፍ ቅዱስ የተመከረ ሐቅ ነው፥ (ዘፍ. @8፥02-05፤ #2፥#)

ቀደምት አበው እግዚአብሔር አምላክ በልዩ ልዩ ራእይ፥ ሕልም፥ አምሳል እየተገለጸላቸው ያለ ምንም መምህር እርሱን ሲያመልኩ ኑረዋል። ድምፁን ሰምተዋል፤ ቃል በቃልም ተነጋግረዋል።

 

5. አስተርእዮ በዝመነ መሳፍንት

ከዘመነ አበው ቀጥሎ ያለው ዘመነ መሳፍንት ይባላል። ጌታ ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ምድር ሲወጡ ጀምሮ መንፈሳዊ ምግብናውን ለካህን፥ ሥጋዊ አስተዳደሩን ለመስፍን ሰጥቶ፥ ካህን ሲሞት ካህን፥ መስፍን ሲሞት መስፍን እየተካ ለብዙ ዘመናት መርቷቸዋል። በዚያ ዘመንም በተለያየ ራእይ በየዘመኑ እየተገለጸላቸው ሲመራቸውና ሕጉን፥ ትእዛዙን ሲገልጽላቸው ኑሯል። ለዚህ ማስረጃ በመጠኑ ለማሳየት ያህል፦

  • ለመጀመሪያው መስፍንና ሊቀ ነቢያት ሙሴ በተለያየ ጊዜ፥ በተለያየ ራእይ መገለጹ፥ (ዘፀ. 3፥1-07፤ 09፥@፤ #4፥@8)
  • ለኢያሱ፥ (ኢያ. 1፥1)
  • ለጌዴዎን፥ (መሳ. 6፥@3፤ 7፥2-0)
  • ለዮፍታሔ፥ (መሳ. 01፥@9)
  • ለሳሙኤል፥ (ሳሙ. 3፥4) … ለመሳሰሉት ሁሉ መገለጹን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ።

6. አስተርእዮ በዘመነ ነገሥት

ከዘመነ መሳፍንት ቀጥሎ ያለው ዘመን፥ ዘመነ ነገሥት ይባላል። በዚህ ዘመን፥ ንጉሠ ነገሥት፥ እግዚአ አጋእዝት፥ መኰንነ ኵሉ ፍጥረት የተባለው አምላካችን እግዚአብሔር በልዩ ልዩ መገለጥ ታይቷል። ይኸውም፦

  • ሥርወ መንግሥት ለተባለው ለንጉሥ ዳዊት መገለጡ፥ ይህ ልበ አምላክ የተባለው ነቢዩና ንጉሡ ዳዊት «ዘልፈ እሬእዮ ለእግዚአብሔር ቅድሜየ ውእቱ በኵሉ ጊዜ እስመ በየማን ውእቱ ከመ ኢይትሀወክ ለዓለም — ሁልጊዜ እግዚአብሔርን በፊቴ አየዋለሁ በቀኜ ነውና አልተውክም» በማለት እግዚአብሔር የተገለጠለት መሆኑን ገልጿል፥ (መዝ. 05፥8)
  • ለጥበበኛው ንጉሥ ለሰሎሞን መገለጹ፥ (ነገ.ቀዳ. 3፥5)
  • ለሌሎችም አበው ቀደምት ነገሥት በየጊዜው በገሃድ፥ በራእይ፥ በሕልም፥ በረድኤት፥ በተአምራት በመሳሰለው ሁሉ ተገልጧል።

7. አስተርእዮ በዘመነ ነቢያት

አስተርእዮ በዘመነ ነቢያት የሚለው ንኡስ ርእስ እጅግ ብዙ መጠነ ሰፊ ዳሰሳ የሚያስፈልገው ነው። ምክንያቱም ጌታ ለቅዱሳን ነቢያት በየዘመናቸውና በየጊዜያቸው በተለያየ ምሳሌ ያልተገለጸለት ነቢይ የለም። የጻፉትም እርሱ የገለጸላቸውንና ያናገራቸውን ነው። በዚህ ጽሑፍም በመጠኑ ለማሳየት ያህል፦

  • ልዑለ ቃል ለተባለው ነቢይ ለኢሳይያስ (ኢሳ. 6፥1-7)፥
  • ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ለመረጠው ለነቢዩ ኤርምያስ፥ (ኤር. 1፥4-9)
  • ለነቢዩ ሕዝቅኤል በፈለገ ባሕር፥ (ሕዝ. 1፥1-@8) …
  • በባዕድ ሀገር ሁኖ አምልኮቱን አጽንቶ ለኖረው ዳንኤል፥ (ዳን. 7፥9)

በመሳሰለው ሁሉ በየጊዜው ለወዳጆቹ ተገልጿል።

ይህ ሁሉ አስተርእዮ የተስፋ፥ የረድኤት፥ የተአምራት፥ የትንቢት፥ የራእይ፥ የሕልምና የመሰለው አስተርእዮ ነው። ዋናውና አማናዊው አስተርእዮ የተስፋውና የትንቢቱ ፍጻሜ ሲደርስ በዘመነ ሥጋዌ የተደረገው አስተርአዮ ነው።

 

8. አማናዊ አስተርእዮ በዘመነ ሥጋዌ

«እግዚአብሔር እግዚእ አስተርአየ ለነ ግበሩ በዓለ በትፍሥሕት በኀበ እለ ያስተሐምምዎ … ጌታ እግዚአብሔር ተገለጸለን፥ በዓልን በደስታ አድርጉ …»  በማለት ነቢዩ ዳዊት እንደተናገረው፥ የእግዚአብሔር መገለጥ በብሉይ ኪዳን ምን እንደሚመስል፥ ማለትም በረድኤት፥ በተስፋ ድኂን፥ በምሳሌ፥ በትንቢት፥ በራእይ፥ በሕልም፥ በገሃድ … በመሳሰለው ሁሉ እንዴት እንደተገለጸ በመጠኑ አይተናል። (መዝ. )08፥@7)

ይህ ሁሉ በተስፋ ሲጠበቅ የነበረው ጊዜ ሲደርስ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ላከ፤ ይህንም ብርሃና ለቤተ ክርስቲያን የተባለው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፦ «ወአመ በጽሐ ዕድሜሁ ፈነወ እግዚአብሔር ወልዶ ወተወልደ እምብእሲት ወገብረ በሕገ ኦሪት — ቀጠሮው በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ላከ፥ ከሴትም ተወለደ፤ በኦሪት የታዘዘውንም ፈጸመ» (ገላ. 4፥4፤ ኤፌ. 1፥0)

ይህ በቀጠሮው ጊዜ የተፈጸመው ተስፋ አበው የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ከሰማይ መላእክትን፥ ከምሥራቅ እጅ መንሻ የሚያቀርቡ ነገሥታትን፥ ከቅርቡ መንጋቸውን የሚጠብቁ ኖሎትን (እረኞችን) በአንድ አሰባስቦ በተአምራት በብርሃን ስቦ አንድ መዝሙር እንዲዘምሩ አደረገ። (ሉቃ. 2፥6)

በዚህ ጊዜ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት «ይገንዩ ቅድሜሁ ኢትዮጵያ፥ ነገሥተ ተርሴስ ወደሰያት አምኃ ያበውኡ ነገሥተ ሳባ ወዐረብ ጋዳ ያመጽኡ ወይሰግዱ ሎቱ ኵሎሙ ነገሥተ ምድር — በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ፤ ጠላቶቹም አፈር ይልሳሉ፥ የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ፤ የሳባና የዐረብ ነገሥታት እጅ መንሻ ያቀርባሉ፤ ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል» ሲል የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ (መዝ. &1፥9-01፤ ማቴ. 2፥1-02)። ቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያውም የዚሁ አማናዊ አስተርእዮ በረከት ተካፋይ ሁናለች። ቀድሞ ንግሥተ ሳባ ለሰሎሞን ንጉሥ ገጸ በረከት እንደሰጠችው እውነተኛው ንጉሥ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜም የኢትዮጵያው ንጉሥ ባዜን እጅ መንሻውን ለጌታ ካቀረቡት ነገሥታት አንዱ እንደነበረ አበው ሊቃውንት በትርጓሜ ዳዊት ገልጸዋል። (መዝ. 71፥9-11)

 

9. አስተርእዮ በፈለገ ዮርዳኖስ

እንዲህም አድርጎ «በበሕቅ ልህቀ በ# ክረምት በዮርዳኖስ ተጠምቀ …» እንዲል በየጥቂቱ አደገ፤ # ዓመት ሲሞላው በፈለገ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ተጠመቀ።

ኮከበ ሊቃውንት፥ ጥዑመ ልሳን ቅዱስ ያሬድ ይህን አስተርእዮ ሲሰብክ «ሐዳፌ ነፍስ ለጻድቃን ቀተስፋ ቅቡጻን ክርስቶስ አስተርአየ ውስተ ዓለም እምድንግል ተወልደ ክሡተ ኮነ እንዘ ይትኤዘዝ ለአዝማዲሁ ከዊኖ ሰብአ በዮርዳኖስ ተጠምቀ — ነፍሳትን የሚያሻግር፥ ተስፋ ለቆረጡት ተስፋቸው ክርስቶስ በዓለም ተገለጠ፤ ከድንግል ተወለደ፥ ለዘመዶቹ ሲታዘዘ ተገልጦ ታየ፥ ሰው ሁኖ በዮርዳኖስ ተጠመቀ» በማለት ይሰብከዋል። (ድጓ ዘዘመነ አስተርእዮ)

ስለዚህ በፈለገ ዮርዳኖስ ስለተፈጸመው አማናዊ አስተርእዮ ነቢዩ ዳዊት አስቀድሞ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ገልጾለት «ባሕርኒ ርእየት ወጎየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ — ባሕርም አይታ ሸሸች፤ ዮርዳኖስም ወደኋላው ተመለሰ» በማለት ዘምሯል። (መዝ. )03፥3)

የባሕረ ዮርዳኖስ ትንቢታዊ ምሳሌና ምሥጢራዊ ትርጒም ከዚህ አስቀድሞ በወጣው የጥምቀት መጽሔት በሰፊው ስለተገለጸ ከዚህ ላይ አልፈዋለሁ።

 

ማጠቃለያ

ከላይ በርእሱ እንደተገለጸው ታላቁ የዜማ አባት ኢትዮጵያዊው የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ይህ የመገለጥ በዓል እንደሚከተለው ገልጾታል «አስተርአየ ዘኢያስተርኢ ኮነ እሙነ አስተርእዮቱ ለመድኀኒነ ክርስቶስ  — የማይታየው ታየ፤ የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መታየቱ እውነት ሆነ። በማለት ስለዚህ ታላቅ የመገለጥ በዓል ዘምሯል (ድጓ ዘአስተርእዮ)፤ ይህንም እንዲሁ ከልቡናው ብቻ አቅንቶ አልተናገረም፤ በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እግዚአብሔር መገለጥ የተጻፈውን መሠረት አድርጎ እንጅ።

ስለዚህ የአስተርእዮ (የመገለጥ በዓል) ከላይ በመጠኑ እንደተገለጸው አስቀድሞ ትንቢት ተነግሯል፥ ምሳሌ ተመስሏል። ልበ አምላክ የተባለው ነቢዩ ዳዊትም ስለዚህ በዓል፦ «ርእዩከ ማየት እግዚኦ፥ ርእዩከ ማየት ወፈርሁ ደንገፁ ቀላያተ ማያት ወደምፃ ማያቲሆሙ — አቤቱ ውኃዎች አዩህ፥ ውኃዎችም አይተው   ሸሹ፤» ብሏል። ይህም በብሉይ በሙሴ ዘመን በባሕረ ኤርትራና በኢያሱ ዘመን በባሕረ ዮርዳኖስ የተፈጸመውን ድንቅ ተአምር የሚያስረዳ ሲሆን፤ በሐዲሱ ሲተረጐም ደግሞ ጌታ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ የተፈጸመውን ድንቅ ተአምር ያስረዳል። (መዝ. &6፥06)

ሐዋርያውም እግዚአብሔር  ለምን (ስለ ምን) እንደተገለጸ ሲያስረዳ «ወበእንተ ዝንቱ አስተርአየ ወልደ እግዚአብሔር ከመ ይስዐር ግብሮ ለሰይጣን … ስለዚህ ነገር የሰይጣንን ሥራ ይሽር ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ» ብሏል። (1ዮሐ. 3፥8)

ከዚህ ከሐዋርያው ትምህርት እንደምንረዳው ይህ የአስተርእዮ (የመገለጥ) በዓል፦

 

  1. ይህ በዓል እግዚአብሔር ወልድ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ በትሕትና ሲጠመቅ የታየበት የትሕትና በዓል ነው፥
  2. ይህ በዓል እግዚአብሔር አብ በደመና ሁኖ «የምወደው ልጄ ይህ ነው …» ብሎ ፍቅርን የሰበከበት የፍቅር በዓል ነው፥
  3. ይህ በዓል እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ በራሱ ላይ ወርዶ ሲቀመጥ የታየበት፥ በዚህ ዕለት በቅንነት ላገለገለ ሁሉ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በሰፊው የሚገኝበት፥ … በአጠቃላይ ምሥጢረ ሥላሴ በገሃድ የተገለጠበት የነገረ ድኅነት መሠረት፥ የመንግሥተ ሰማያት መግቢያ በር የሆነችው ምሥጢረ ጥምቀትን ጌታ በተግባር የፈጸመበት (ያስተማረበት) ዕለት ስለሆነ በዓሉ እጅግ ታላቅ በዓል ነው።

በዓለ አስተርእዮ የመገለጥ በዓል ስለሆነም ታቦተ ሕጉ ከቤተ እግዚአብሔር ወደ ጥምቀተ ባሕር ወርዶ፥ በካህናት በሊቃውንት፥ በመዘምራንና በምእመናን ታጅቦ ከባሕረ ጥምቀቱ ሲደርስ በተዘጋጀለት ድንኳን ያድራል።

ለበዓሉ የሚገባው አገልግሎት ሲፈጸም አድሮ ቅዳሴ ከተቀደሰ በኋላ ባሕረ ጥምቀቱ ይባረካል። ባሕረ ጥምቀቱ ተባርኮ ሕዝቡ ከተጠመቀ በኋላ ታቦተ ሕጉ በከፍተኛ ድምቀት በያሬዳዊ ዜማና በልዩ ልዩ አገልግሎት ታጅቦ ወደ መንበረ ክብሩ ይመለሳል።

በዚሁ በዘመነ አስተርእዮ ከሚከበሩ በዓላት መካከል የእመቤታችን የዕረፍቷ በዓል «አስተርእዮ» ይባላል።

 

በጥምቀቱ ውኃን ለጥምቀታችን የቀደሰልን አምላካችን ይክበር ይመስገን፤ አሜን።

 

መጋቤ ምሥጢር ፍሬ ስብሐት ዱባለ

የሊቃውንት ጉባኤ ም/ሰብሳቢ