በቦሰት ወረዳ ቤተ ክህነት የመርቆ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ፡መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ባልታወቁ የታጠቁ ኃይሎች ተቃጥሏል፡፡

በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በቦሰት ወረዳ ቤተ ክህነት የመርቆ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን በአሳዛኝ ሁኔታ ባልታወቁ የታጠቁ ኃይሎች ትናንት ጥር 17/2016 ዓ.ም አመሻሽ ላይ ተቃጥሏል፡፡

“ችግር እና መከራ ሁሉ ጊዜያዊ ነው፤ በእምነት በመጽናት ችግርን የምናልፍ አስተዋዮች መኾን አለብን”ብፁዕ አቡነ አብርሃም

በየዓመቱ በባሕር ዳር ከተማ በድምቀት የሚከበረው” የቅዱስ ጊዮርጊስ ስባር አጽሙ” ሃይማኖታዊ በዓል ዛሬም በድምቀት እየተከበረ ነው።

የዴንቨር ኮሎራዶና አካባቢው ሀገረ ስብከት ፮ኛው የሰበካ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ በመካሔድ ላይ ነው።

በሰሜን አሜሪካ በዴንቨር ከተማ በዛሬው ዕለት የሀገረ ስብከቱ ፮ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መካሔድ ጀመረ። በ፮ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ የተገኙት የዴንቨር ኮሎራዶና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ጉባኤውን በፀሎት የከፈቱት ሲሆን ጉባኤውንም በርዕሰ መንበርነት እየመሩት ይገኛሉ።

በጋምቤላ ሀገረ ስብከት በጋምቤላ ከተማ ባሕረ ጥምቀት ለአምስት ቀናት ሲካሄድ የሰነበተው የስብከተ ወንጌል ጉባኤ ተጠናቀቀ።

ከበዓለ ጥምቀት ማለትም ከጥር 10 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሲከናወን የሰነበተው የስብከተ ወንጌልና የመዝሙር አገልግሎት በደመቀ ዝግጅት ተጠናቋል።

የ፳፻፲ወ፮ ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስ የጥምቀት በዓል አከባበር በጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት አምስቱም ሀገራት በጀርመን፣ በኔዘርላንድ፣ በስዊዘርላንድ፣ በኦስትሪያ እና በፖላንድ ባሉ ወረዳ አብያተ ክህነትና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በጥምረትና በድምቀት ተከበረ ።

በዓሉ በተለይ በጀርመን ሔሰን ግዛት ፍራንክፈርት ከተማና አካባቢው ያሉ አራት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በጥምረት በደብረ ኀይል ቅዱስ ዑራኤል ወቅዱስ ያሬድ ቤ/ክ አዘጋጅነት ጥር ፲፪ ቀን የ፳፻፲ወ፮ ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ የጀርመንና አካባቢው እና የምሥራቅ ጎጃም አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት በማኅሌት በቅዳሴ ሥርዓተ ጥምቀቱን በመፈጸም በድምቀት ተከብሮ ውሏል ።

በጋምቤላ ሀገረ ስብከት በጋምቤላ ከተማ የመድኃኔ ዓለም እና የአቡነ አረጋዊ ታቦታተ ሕግ ወደመንበረ ክብራቸው በሰላም ገብተዋል።

ጥር 14 ቀን 2016 ዓ.ም

የከተራ፣የጥምቀትና የቃና ዘገሊላ በዓላት በአላማጣ በድምቀት ተከብሮ ዋለ።

የከተራ፣የጥምቀትና የቃና ዘገሊላ በዓላት በራያ አላማጣና በስድስቱ ወረዳዎች በታላቅ መንፈሳዊ ሥነሥርዓት ተከብሮ መዋሉን የሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት በላከልን ዘገባ ገለጸ።ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ተወልደው ባደጉበት ራያ አላማጣ ከተማ ከሦስት ዓመታት በኋላ በዓላቱን እንዳከበሩ የገለጸው የሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት ሕዝበ ክርስቲያኑ በነቂስ በመውጣት በዓሉም ፍጹም ሰላማዊና ደማቅ በሆነ መልኩ ማክበሩን ገልጿል።

የ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም የጌታችን፣ የአምላካችን፣ የመድኀኒታችን፣ የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል ሰላማዊ በሆነ መልኩ ተከብሮ እንዲውል ላደረጋችሁ ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምስጋናዋን ታቀርባለች፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም የጌታችን፣ የአምላካችን፣ የመድኃኒታችን፣ የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም ተከብሮ እንዲውል ለማድረግ ልዩ ልዩ ኮሚቴዎችን በማቋቋም ስትሠራ የሰነበተች ሲሆን ከሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል መንግሥታትና የጸጥታ አካላት ጋርም በመነጋገር በዓሉ ያለ አንዳች የጸጥታ ችግር ተከብሮ እንዲውል ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ ሰንብታለች።

በዚህም  መሰረት የከተራ፣ የጥምቀት፣ የቃና ዘገሊላ፣ የቅዱስ እግዚአብሔር አብ እና የቅዱስ ሩፋኤል በዓላት ፍጹም ሰላማዊና ሃይማኖታዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በተረጋጋ፣ መንፈሳዊ በሆነና ፍጹም ክርስቲያናዊ ግብረ ገብነትን በጠበቀ ሁኔታ በመላ አገራችን ተከብሮ ውሏል። በተለይም በአዲስ አበባ በጃን ሜዳ በማዕከል ደረጃ የተከበሩት በዓላት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቀ አእላፍ በላይ መኮንን የጠቅላይ ቤተክህነት ምክትል ሥራአስኪያጅ፣ የፌደራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣የጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፣ ሊቀ ማዕምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች፣ በሚሊየን የሚቆጠሩ ምእመናንና ምእመናት በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ውሏል።

የ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም የጥምቀት በዓል በዚህ መልኩ ባማረና በደመቀ ሁኔታ ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ ምዕመናንና ምዕመናት እንዲሁም ወጣት የቤተክርስቲያን ልጆቻችን የቤተክርስቲያንን ድምጽ በመስማትና በማክበር ላደረጋችሁት ከፍተኛ ጥረት ቅድስት ቤተክርስቲያን ምስጋናዋን ታቀርባለች። በዓሉ ያለምንም የጸጥታ ችግር ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ ቀን ከሌሊት የጸጥታውን ሥራ በማከናወንና አመራር በመስጠት፣ የትራፊክ ፍሰቱ በዓሉን በማያውክ መልኩ እንዲከናወን ያደረጋችሁ የከተማችን አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች፣ የጸጥታ አካላቱ አመራሮችና የጸጥታ መዋቅሩ አባላት እንዲሁም የትራፊክ ፓሊስ አመራሮችና አባላቱ ላበረከታችሁት አስተዋጽኦ ቅድስት ቤተክርስቲያን ልባዊ ምስጋናዋን ታቀርባለች።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት አዳነች አቤቤ በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲውል ለሰጡት አመራርና በዓሉ በተከበረበት በጃንሜዳ ደረጃውን የጠበቀ ስቴጅ፣ የድምጽ መሣሪያ፣ የክብር እንግዶች ወንበርና ለበዓሉ ድምቀት የሚያስፈልገውን ሁሉ በማሟላትና ወጪውን በመሸፈን በዓሉ አገራዊ መሆኑን በተግባር በማሳየት ላደረጉልን ድጋፍ በድጋሚ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ልባዊ ምስጋናዋን ታቀርባለች።

በአጠቃላይ የ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም የጥምቀት በዓላችን ፍጹም መንፈሳዊና ደማቅ በሆነ መልኩ ተከብሮ እንዲውል ልዩ ልዩ ድጋፍ ያደረጋችሁ አካላትና የተለያዩ ዕምነት ተከታይ ወገኖቻችን ያደረጋችሁትን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ቤተክርስቲያናችን በልዩ አድናቆት የምትመለከተው ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ  ምስጋናዋን ታቀርባለች። ወደፊትም በመሰል የአደባባይ በዓላቶቻችን ላይ በጋራ መሥራታችንን አጠናክረን እንድንቀጥል አደራ ትላለች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት
ጥር ፲፫ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ

በዓለ ጥምቀትን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች የቤተክርስቲያን አስተምህሮ ላይ ብቻ ያተኮረ ምላሽ እንዲሰጥ መመሪያ ተላለፈ።

በዓለ ጥምቀትን አስመልክቶ የሚተላለፉ መልእክቶች የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ ላይ ብቻ ያተኮሩ እንዲሆኑ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የባህር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መመሪያ አስተላልፈዋል።

የ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም የጥምቀት በዓል አከባበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ ናቸው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት መካከል የጥምቀት በዓል አንዱና ዋነኛው ነው። በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው የአደባባይ መንፈሳዊ በዓላችን የጥምቀት በዓል ዘንድሮም በታላቅ ሥነሥርዓት የሚከበር ሲሆን በዓሉ በደመቀና ባማረ መልኩ ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሰብሳቢነት ዐቢይ ኮሚቴ ተጀራጅቶ በየዘርፉ የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት ላይ ይገኛል።