ለሦስት ወራት በ6 አህጉረ ስብከት ሲካሄድ የነበረው ሐዋርያዊ ጉዞ ለቤተክርስቲያን ዘርፈ ብዙ ትርፎችን በማትረፍ ተጠናቀቀ
ጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም.
+ + +
የጋምቤላ ፣ የቄለም ወለጋ፣ የአሶሳ፣ የምዕራብ ወለጋ ፣ የሆሮ ጉድሩ ፣ የምስራቅ ወለጋ እና የደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ የጋምቤላ ክልል እና የቤኒ ሻንጉል ክልል የሰላምና የልማት አንባሳደር ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ከሐምሌ 2016ዓ.ም. ጀምሮ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉዞ በህገ ወጡ ሹመት ምክንያት ወደ ሕግ ያልገቡ አህጉረ ስብከቶችን ወደ ሕግ ከማስገባት ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ቱሩፋቶችን ለቤተክርስቲያን በማትረፍ ሐዋርያው ጉዟቸውን ማጠናቀቃቸውን የምስራቅ ወለጋ ሀገረ ስብክት ሕዝብ ግንኙነት ክፍል አስታወቀ።
ብፁዕነታቸው በሁሉም አህጉረ ስብከት የቤተክርስቲያንን አንድነት በማስጠበቅና ሥርዓትን በመዘርጋት ዘርፈ ብዙ ውጤት ያሳዩ ሲሆን ከጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ሕገ ወጥ ሹመት በኋላ ከሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተሳታፊነት ተለይተው የነበሩት የሦስቱ ወለጋ አህጉረ ስብከት በዘንድሮው ዓመት በሚከበረው 43ኛው የሰበካ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከየሀገረ ስብከቱ ሰባት ሰባት ልዑካን ተወክለው ወደ መንበረ ፓትርያርክ እየመጡ እንደሆነ ተገልጿል።
የ7ቱ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሐዋርያዊ ጉዟቸው ማጠናቀቂያ ላይ በጊንቢ ከተማ በአቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም ጸሎተ ኪዳነ አድርሰው የጉዟቸው መጀመሪያ አድረገውት ወደነበረው ምስራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት በማቅናት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅና የየክፍል ኀላፊዎች፣ የሆሮ ጉድሩ አህጉረ ስብከት ዋና ሥራ አሥኪያጅና የየክፍል ኀላፊዎች በነቀምቴ ከተማ የሚገኙ የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች ሊቃውነተ ቤተክርስቲያን እና የሰንበት ትምርት ቤት ወጣቶች በተገኙበት ህገ ቤተክርስቲያንን ጠብቆ በማስጠበቅ ረገድ መመሪያ ሰጥተዋል።
በ42ኛው የሰባካ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ያልበሩት ምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮ ጉድሩና ምዕራብ ወለጋ አህጉረ ስብከት ወደ እናት መንበራቸው በመመለስ ከጥቅምት 4-10 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የሚከበረውን 43ኛው የሰበካ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ የበጀት ዓመቱን ቅጽ በመሙላት ከብፁዕነታቸው ጋር በመሆን ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ጀምረዋል።
ብፁዕነታቸውና የሀገረ ስብከቱ ልዑካን ወደ መንበረ ፓትርያርክ ሲያቀኑ በነቀምቴ ከተማ የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች ፣ ካህናት ፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እና ምዕመናን ሽኝት አድርገውላቸዋል።
ዘገባውን ያደረሰን የሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግንኙነት ነው።