ታኅሣሥ 13 ቀን 2017 ዓ.ም
በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት የቆቦ ከተማ አስተዳደር ቤተክህነት ለአብያተክርስቲያናት አገልጋዮች በዘመናዊ የሒሳብ አሠራርና በእቅድ አዘገጃጀት ላይ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል።

በሀገረ ስብከቱ ተዘጋጅቶ እስከአጥቢያ አብያተክርስቲያናት የወረደው መሪ እቅድ የሚተገበረው በታችኛው መዋቅር በመሆኑ አገልጋዮች ግንዛቤው ኖሯቸው ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ሥልጠና መሆኑን የቆቦ ከተማ አስተዳደር ቤተክህነት ዋና ጸሐፊ መጋቤ ሃይማኖት ሳሙኤል ፈለቀ ተናግረዋል።
ዘመናዊ የሒሳብ አሠራርን በመተግበር ገንዘብን መቆጣጠርና ሀብትን በአግባቡ መጠቀምን በተመለከተ በሀገረ ስብከቱ ቁጥጥር ክፍል ኀላፊ ሊቀ ጉባኤ ብርሃን ደመቀ ግንዛቤ ተፈጥሯል።

የሀገረ ስብከቱ እቅድና ፕሮጀክት ዝግጅት ባለሙያ አቶ ስጦታው አድማሴ በበኩላቸው በእቅድ ዝግጅት፣ ክትትል፣ ግምገማና የሪፖርት አዘገጃጀት ላይ ሥልጠና የሰጡ ሲሆን በመሪ እቅዱ ላይ ተቀራራቢ ግንዛቤ አንዲኖር ማድረግ፣ ለአገልግሎት ግልጽና የተሳለጠ ተግባቦት መፍጠርን ታሳቢ ተደርጓል ተብሏል።
የቆቦ ከተማ አስተዳደር ቤተክህነት ሠራተኞች፣ የ25 አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የሰበካ ጉባኤያት ጸሐፊዎች ሒሳብ ሹሞች፣ ገንዘብ ያዥዎችና የእቅድ ኮሚቴዎች በሥልጠናው ተሳትፈዋል።
በግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናው ከ120 በላይ አገልጋዮች መሳተፋቸውን የከተማ አስተዳደር ቤተክህነቱ ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።