በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

•ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት
ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባሕር ዳር ሀገረ
ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
•ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና
ጸሐፊ እና በሰሜን አሜሪካ የኒዮርክ እና
አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
•ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ
አባላት፤
ሁሉንም ጠብቆ የሚያስጠብቅ እግዚአብሔር አምላካችን ከተሠማራንበት የጥበቃ ስፍራችን አሰባስቦ በደሙ ስለዋጃት ቅድስት ቤተክርስቲያን እንድንመክር ስለፈቀደልን ምስጋና ለእሱ እናቀርባለን፣ እናንተም እንኳን ደኅና መጣችሁ ለማለት እንወዳለን፡፡
“ወዘእንበለዝ ብዙኅ ባዕድ ዘረከበኒ ኲሎ አሚረ እንዘ እኄሊ ቤተ ክርስቲያናት፡- የቀረውንም ነገር ሳልቈጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ሐሳብ ነው” (2ኛ ቆሮ 11፦28)
ከዚህ ጥቅስ እንደምናስተውለው ከስራ ሁሉ የሚያስጨንቅ ተግባር የቤተ ክርስቲያን ነገር እንደሆነ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሚገባ አስቀምጦአል፡፡ እርግጥ ነው ሌሎች የሚያስጨንቁ ችግሮች በዓለም አሉ  ግን ሌሎቹ ለጊዜውም ቢሆን ባላቸው ማቴሪያላዊ ኃይል ማስታገሥ ይችላሉ፡፡ ቤተክርስቲያን ግን ከመንፈስ ቅዱስ ከተሰጠ ረቂቅ ኃይለ መዊዕ በቀር ሌላ ማቴሪያላዊ ኃይል የላትም አይፈቀድላትምም፡፡
ይሁን እንጂ ከኃይል ሁሉ የበለጠ ኃይል እንዳለን ጌታችን ነግሮናል እኛም እናውቀዋለን፡፡ ነገር ግን የኛ ድክመት ኃይሉ እንደሚፈለገው እንዳይሰራ ያደርገዋል ይህም እውነት ነው የተሰጠን ኃይል በእኛ ድክመት የተቀዛቀዘ ቢመስልም የማይሸነፍ ነውና ኃይላችንን አውቀን ካልተጠቀምንበት እኛንም ጭምር ቀጥቶ የበላይ አሸናፊነቱን ያረጋግጣል ይህም የታየ እውነት ነው፡፡
ስለሆነም ሐዋርያው እንዳለው በውስጣችን ያለው ኃይል አቀጣጥለን ሙሉ በሙሉ መጠቀም እንችል ዘንድ ራሳችንን ክደን ለእግዚአብሔር ክብርና ለቤተክርስቲያኑ ተልእኮ በአንድነት መቆም የግድ ይላል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ያለ መከራ አልኖረችም ለወደፊትም ከዚያ የተለየ ዕድል አትጠብቅም፡፡ ለምን ቢባል ጥበበኛው ሰሎሞን እንደነገረን “በእሾኽ መካከል ያበበች የሃይማኖት አበባ” ናትና ነው፡፡ ጌታችንም ስለ ስሜ በሁሉም ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ ያሳድዱአችኋል፣ይገርፉአችኋል፣ ይገድሉአችሁማል ብሎ ዕቅጩን ነግሮናል፡፡
ዓለም እንደ ካሁኑ በፊት አሁንም በእሾኽነትዋ ቤተ ክርስቲያንን እየወጋች ነው ታዲያ ከመጽናት በቀር ከኛ ሌላ ምን ይጠበቃል?
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ወኤጲስ ቆጶሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!!
እኛ ያለንበት የመልክዐ ምድር አቀማመጥ እጅግ ፈታኝ ነው፡፡ ዓለም እኛን ለመጥቀም ሳይሆን ለራሱ ሲል የሚቀራመተው አካባቢ ነው፡፡ ለዚያ ሲባል የደረሰብንም ጫና ምን ያህል እንደሆነ የምንስተው አይደለም እኛም አንድነታችንንና ወንድማማችነታችንን አጽንተን መቆም ባለመቻላችን ለአደጋው ይበልጥ ተጋላጭ ሆነናል፡፡
ሕዝብ ተጐዳ ማለት ቤተክርስቲያን ተጐዳች ማለት እንደሆነ አንርሳው ቤተክርስቲያን ማለት በዋናነት ሕዝበ ክርስቲያን ነውና፡፡ ያለንበት አካባቢ ለልዩ ልዩ ጥቃት የተጋለጠ ሆኖ ሳለ ቤተክርስቲያናችን ለሁለት ሺሕ ዓመታት ያህል ብቻ ለብቻ ሆና በሃይማኖተ ክርስትና መዝለቋ እጅግ የሚያስደንቅ መሆኑን እናስታውስ፡፡
ይህ የሚያሳየው የቀደምት አባቶቻችን ጽንዐ ሃይማኖትና ጥንካሬ ስለሆነ ሳናመሰግናቸው ብናልፍ ትልቅ ኃጢአት ይሆንብናል እነሱን ማመስገንም በቃላት ብቻ አይሆንም፡፡
እነሱ የሰሩትን በመጠበቅና በመድገምም እንጂ ለዚህ ተልእኮ ይህ ጉባኤ ኃላፊነት አለበትና ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ይኖርበታል፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ወኤጲስ ቆጶሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!!
ከሁኔታዎች በትክክል መገንዘብ እንደሚቻለው ቤተክርስቲያናችን ከሚተቻት ይልቅ የሚወዳት ይበልጣል  በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ፈላጊዎቿ ብዙ ናቸው፡፡ ለዚህ ተጠቃሽ የሚሆኑን በሀገር ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ እንደዚሁም በአፍሪካና በላቲን አሜሪካ የሚገኙ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ለነዚህ ሕዝቦች ፈጣንና ዘላቂነት ያለው ግብረ መልስ ከዚህ ጉባኤ ይጠበቃል ይህ በቀጣዮቹ ዓመታት በመሪ ዕቅዱ መሠረት በስፋት የምንሰራው ስራ ይሆናል፡፡
ቤተክርስቲያን በዓሥር ሚሊዮኖች የሚቈጠሩ ተከታዮች በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ያሏት በመሆኗ የሀብት ዕጥረት ያጋጥማታል ተብሎ አይጠረጠርም፡፡ ምክንያቱም ትልቁ ሀብት ሰው ስለሆነ ሰውን በቃለ ቅዱስ ወንጌል በሚገባ ከገነባች፣ አስተዳደርዋና የሀብት አያያዟ በትክክልና በሓቅ ጠብቃ ለሚገባው የሃይማኖት ተልእኮ ለማዋል የሚያስችል አሰራር ከዘረጋች  ይህንንም በምእመናን አእምሮና ዓይን ከተረጋገጠ እንኳን ለገንዘቡ ለሕይወቱ የማይሳሳ ምእመን እንዳላት ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ታድያ ሀብት ማለት ይህ አይደለምን? አሁን መስራት ያለብንስ ይህ ሀብት በትክክል መጠበቁ ላይ አይደለምን?
ይህም በቀጣዩ ዓመት በስፋት የሚሰራበት ይሆናል  የዕቅበተ ንዋይ፣ የዕቅበተ ሃይማኖት፣ የሥልጠናና ትምህርት፣ የገዳማትና ቱሪዝም፣ የምርትና የደን ሀብት፣ የፋይናንሱ ሴክተርና የስብከተ ወንጌሉ ተልእኮ ዘመኑ በሚጠይቀው የአመራርና የአሰራር ጥበብና ስልት እየታገዝን፣ ሕዝባችንንም ከጎናችን እያሰለፍን የምንሰራበት ጊዜው አሁን ነው፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ወኤጲስ ቆጶሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!!
ለጀመርናቸውና ለወደፊት ለምንጀምራቸው የመልካም አስተዳደርና የልማት ስራዎች ዋስትና እንደሚያስፈልጋቸው እሙን ነው፡፡ የስራዎቻችን ዋስትናም በሀገርና በቤተክርስቲያን ፍጹም የሆነ ሰላምና አንድነት መኖር ነው፡፡ በመሆኑም የጠማንን ሰላምና አንድነት መልሶ ለማምጣት የቤተክርስቲያን ኃይል የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ሆኖም የቤተክርስቲያን የሰላም ጉዞ ከማንኛውም ወገንተኝነት በጸዳ፣ ማእከሉና ዓላማው የሀገርና የቤተክርስቲያንን አንድነት ብቻ መሠረት ያደረገ መሆን ይገባዋል
ከዚህ አንጻር በሀገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በቤተክርስቲያናችንም እንከን የለሽ አንድነት እንዲረጋገጥ በብርቱ መስራት ይኖርብናል፡፡ አኲርፈው የተለዩትን በጠባይ ወደ እኛ እናምጣቸው እኛም ኲርፊያን ከሚያስከትል ድርጊት እንራቅ በአንድነት፣ በእኩልነትና በጋራ ሆነን ታላቋን ቤተክርስቲያን እንሰብስብ፣ እናገልግል፣ እንምራ፣ እንጠብቅ፡፡
ለዚህም ሙሉ ዝግጅት እናድርግ የዕለት ተዕለት ስራችን የቤተ ክርስቲያንን ጭንቀት የሚያቃልል ይሁን ይህ ከሆነ ቤተ ክርስቲያንን ያለምንም ጥርጥር በዕድገት ጐዳና ወደፊት እናሻግራለን፡፡
በመጨረሻም
የታላቋን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን መርምሮ ገምግሞና አጥንቶ ችግር ፈቺ ውሳኔን የመስጠት ኃላፊነት ያለው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት የተከፈተ መሆኑን በቤተክርቲያን ስም እናበስራለን፡፡ እግዚአብሔር የተባረከና የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን!

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
አሜን፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥቅምት 12 ቀን 2016 ዓመተ ምሕረት
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ