በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት ዋና ስራ አስኪጅ፣ የባሕር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፣የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣
ክቡር——————————————————————–
ክብርት —————————————————————-
ክቡራን የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣
ክቡራን አምባሳደሮችና የኮር ዲፕሎማቶች፣
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የየመምሪያው ኃላፊዎች፣
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣
የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች፣
በአጠቃላይ በቅርብና በሩቅ ሆናችሁ የ2017 ዓ.ም በዓለ ጥምቀት እያከበራችሁ የምትገኙ ሕዝበ ክርስቲያኖች በሙሉ፣
በመጠመቁ የክዋኔ ልጅነቱን አስመስክሮ የጸጋ ልጆች እንድንሆን ያበቃንን ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ሰባት ዓመት ምሕረት የጥምቀተ ክርስቶስ በዓል አደረሰን አደረሳችሁ፡፡
ወመጽአ ቃለ እግዚአብሔር ኀበ ዮሓንስ ወልደ ዘካርያስ፤የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሓንስ መጣ (ሉቃ ፩÷፪፤)
የመሲሑ መንገድ ጠራጊ ሆኖ እንዲያገለግል በእግዚአብሔር ዘንድ ከዘመናት በፊት የተመረጠው ዮሓንስ ወልደ ዘካርያስ ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ነበር፤ ቅዱስ ዮሓንስ በዮርዳኖስ በረሃ በብሕትውና ሕይወት በነበረበት ወቅት የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ፤ ወደ እርሱ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ የሚል ነበር፡-
‹‹የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አቅኑ፣ዓዘቅቱ ሁሉ ይሙላ፤ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል፤ ጠማማውም የቀና መንገድ ይሁን ፤ሸካራውም መንገድ ይስተካከል፤ ሥጋም የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ››፤
መጥምቁ ዮሓንስ ይህንን የድኅነት መልእክት ከእግዚአብሔር የመጣለት በገዳመ ዮርዳኖስ ባሉ ከተሞች እያስተማረና ሕዝቡን ለንስሐ እያዘጋጀ በነበረበት ጊዜ ነው፤ የትምህርቱ ዋና ይዘትም የጌታ መንገድ የሰው አእምሮ መሆኑን በማስገንዘብ ጌታ በዚህ መንገድ እንዲጓዝበትና እንዲመላለስበት በደንብ ይዘጋጅ የሚል ነው፤
የዝግጅቱም ሁናቴ በዝርዝር ሲገለጽ ተስፋ በመቁረጥ እንደ ዓዘቅት የጐደጐደውና የጨቀየው አእምሮ በተስፋ ድኂን ቀና ይበል፤
በሥልጣን፣ በዕውቀት፣በሀብትና በወገን ከሁሉ የላቀ እንደሆነ የሚያስብም እንደማንኛውም ሰው መሆኑን ተረድቶ እኩልነትን ተቀብሎና ኣክብሮ ይኑር፤ በክፋትና በምቀኝነት፣ በተንኮልና በሴራ አተርፋለሁ የሚል ጠማማ አእምሮም ወደ ቅን አስተሳሰብ ይመለስ፤ በቂም፣ በበቀልና በጥላቻ ተዘፍቆ የሚኖር ልብም በሰላም በፍቅርና በስምምነት ወደሚገኝ የተስተካከለ ጣዕመ ሕይወት ይግባ ማለት እንደ ሆነ እናስተውላለን፤
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣
የተከበራችሁ የበዓሉ ተሳታፊዎች!
እግዚአብሔር ምድርና ሰማየ ሰማያት የማይችሉት ምሉእ፤ረቂቅና ስፉሕ ነው፤
ይሁን እንጂ በቅዱሳን ሰዎች አእምሮ ውስጥ ማደርና ማረፍ በእጅጉ የሚሻ አምላክ እንደሆነ ደጋግሞ ገልጾአል፤መመላለሻውም በሰው ኅሊና፣ በሰው ልቡና እና አእምሮ ውስጥ እንደሆነ አልሸሸገም፤ያም በመሆኑ መንገዱና ጥርጊያው የሆነ የእኛ አእምሮ ቀጥ ያለና ይማይጐረብጥ እንዲሆንለት ያዘናል፤
መጥምቁ ዮሓንስም ይህ ዓይነቱ ዝግጅት በሰው አእምሮ ውስጥ እንዲኖር ለመቀስቀስ ተልኮአል፤
ዝግጅቱ የጠቅላላ ስራው መቋጫ አልነበረም፤ የዝግጅቱ ዋና መቋጫ ሰው ሁሉ እንደ ስምዖን የእግዚአብሔርን ማዳን በዓይኑ አይቶ በአእምሮው አስልቶ በልቡ ኣምኖ የድኅነቱ ባለቤት መሆን ሲችል ነው፤ የእግዚአብሔር ፈቃድና ፍላጎትም ይኸው ነው፤ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የኛን ሰውነት በመዋሐድ አምላክና ሰው ሆኖ በዚህ ዓለም እንዲገለጥ ያስፈለገበት ዓቢይ ምክንያትም ይኸው ነው፤ ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ በዛሬው ዕለት በፈለገ ዮርዳኖስ የፈጸመው ምስጢረ ጥምቀት ሰው የሚያድንበት ዕድል ምን እንደሆነ ለማስረዳት ነው፤
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣
የተከበራችሁ የበዓሉ ተሳታፊዎች!
ሰው በራሱ ዘላቂ ሕይወት የለውም፤ የሕይወት ምንጭ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ ሰው ዘላቂ ሕይወትን ማግኘት የሚችለው የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር ልዩ ግንኙነት ሲኖረውና በግንኙነቱ አማካኝነት ዘላዓለማዊ ሕይወት ከእግዚአብሔር ሲቀዳጅ ነው፤ ይህንንም ልዩ ግንኙነት የሚያገኘው ከእግዚአብሔር ሲወለድ ነው፤ ለመወለድ ደግሞ በእግዚአብሔር የማዳን ስራ ማመንና መጠመቅ ሲቻል ነው፤ ሰው ሲጠመቅ የእግዚአብሔር ልጅ ይሆናል፤
እግዚአብሔርም በልጁ አእምሮ ውስጥ በሃይማኖት በአምልኮና በምስጋና ይመላለሳል፤ ያድራል፤ ያርፋልም፤ ሥጋ የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ የተባለውም ይህንን ልጅነት ነው፤
በዚህ ልጅነት ምክንያት ሰው የዘላለም ሕይወት ባለቤት ሆኖ ይኖራል፤ ጥምቀት ለሰው ልጆች የሚያስገኝልን ጸጋ ይኸው ነው፤
ታዲያ የእግዚአብሔር የዝግጅት ጥሪ ዘላዓለማዊ ሕይወትን ለማደል ሆኖ ሳለ የተጠበቀው ዝግጅት ግን ከሰው እየታየ ኣይደለም፤
ዛሬም እኛ ሰዎች አእምሮችን ጐድጓዳ ዓዘቅት ሆኖ በመቀጠሉ ለጉዞ አልተመቸውም፤
ዛሬም ልባችን ከተራራና ኮረብታ ባልተናነሰ ሁናቴ ትዕቢት እንደተሞላ ነው፤ ከቅንነት ይልቅ ጠማማነት፤ ከእውነት ይልቅ ማሴር የየዕለት ተግባር አድርገነዋል፤
በዚህም እግዚአብሔር ከኛ እንዲርቅ አድርገናል እሱም በኣጸፋው ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጥቶናል፤ ዓለማችን በአሁኑ ጊዜ ያላት ምስል ይኸው ነው፤
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣
የተከበራችሁ የበዓሉ ተሳታፊዎች!
ዓለማችን አሁን ያለችበት ምስል ለሰው ልጅ ሁሉ በጣም አሳሳቢና አስፈሪ ነው፤ ለእግዚአብሔር አልታዘዝም ብሎ በነውረ ኃጢአት መጋለብና ለጦርነትና ለዕልቂት የሚሆን መሳሪያ በማምረት መሽቀዳደም የሚበጅ አይደለም፤
ከዚህ ይልቅ ዓለማችን አሁንም ቆም ብላ ብታስብና ሕይወት ወደ ሆነው እግዚአብሔር እንድትመለስ በእግዚአብሔር ስም እንመክራለን ፤
በሰው ልጆች የሚታይ መሠረታዊ ችግር ከእግዚአብሔር መለየትና ለእሱ ያለመታዘዝ እንጂ የሀብት ዕጥረት አይደለም፤
ምድሪቱ ኁልቈ መሥፈርት የሌለው ሀብት በውስጥም በውጭም አጭቃ ይዛለች፤ እሱን በፍቅርና በስምምነት ብናለማው ከበቂ በላይ ነው፤
እሱም ቀርቶ ያለውን ለጦርነትና ለዕልቂት ከምናውለው ለልማት ብናውለው ችግርና እጦት ከምድራችን በጠፋ ነበር፤
አሁንም ራሳችንን በራሳችን ከማጥፋት ተቆጥበን የምድራችንን የአየር ንብረትና የተፈጥሮ ሥነ ምኅዳር በመጠበቅ ግጭትንና ጦርነትን በማስቆም ለተመደበልን ሰላማዊ ሕይወት ልንተጋ ይገባል፣
በመጨረሻም
በዓለ ጥምቀቱ ከእግዚአብሔር የምንወለድበትን ዕድል የከፈተ ነው፤ በዚህም ዕድል የእግዚአብሔር ልጆች ለመሆን በቅተናል፤
ስለሆነም የእግዚአብሔር ልጆች ለመሆናችን ልዩ ምልክታችን የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የፍትሕና የእኩልነት ሰዎች ሆነን እንድንገኝ ነውና በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያላችሁ ልጆቻችን ሁሉ በሃይማኖት ጸንታችሁ ለሰላምና ለአንድነት ከምንጊዜውም በላይ የበኩላችሁን ጥረት ታደርጉ ዘንድ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡
በዓለ ጥምቀቱን የሰላምና የበረከት ያድርግልን
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ
ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣
ጥር ፲፩ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ