በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ  አሐዱ አምላክ አሜን!

“የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” (ኢሳ.9፥6)

ክቡራትና ክቡራን የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ በ7ቱም አህጉረ ስብከት በየደረጃው የምታገለግሉ ካህናት መምህራን፤ የሰበካ ጉባኤ አባላት፤ የሰ/ት/ቤት መዘምራን፤ ወጣቶች የመንፈሳዊ ማኅበር አባላት፤መላው ህዝበ ክርስቲያን በመጀመሪያ እንኳን ቸሩ አምላካችን እግዚአብሔር በሰላምና በጤና ጠብቆ ለ2017ኛው ዓመት ለጌታችንና የመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት አደረሳችሁ አደረሰን!

የሰላም አለቃ ማለት ሰላም የባሕርይ ገንዘቡ የሆነች ከማንም የማይፈልጋት ከእርሱ የምትመነጭና ለሚፍልጓት ሰዎች ሁሉ የሚሰጣት ሰላም የባሕርዩ መገለጫ የሆነ ማለት ነው።

የሰላም አለቃ የሆነውን ጌታ ከመከተልና እርሱን ከማምለክ የራቀች አለቅነቱን ያልተቀበለች፣ ግዛቱ ዘላለማዊ መሆኑን የዘላለም ንጉሥነቱን አላውቅም እንቢ ያለችው ይህች ዓለም የሰላም አለቃ ሆኖ የተወለደውን ፤ የሰላም ንጉሥ ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስን አሳልፋ ለሞት ስለሰጠች ሰላም እርቋት ከቆዬ ዘመናት ተቆጥረዋል።

ዓለም ስለሰላም አብዝታ ብትጮህም የሰላምን ምንጭ ስላደረቀችውና ሰላም ከማይገኝበት ቦታ ስለምትፈልግ አልተሳካላትም።

የሰው ልጅ ሰላም እርቆት፤ ጨለማ ውጦት በነበረበት ዘመን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰላም አለቃ ሆኖ ተወለደ ፤ ነብዬ ልዑል ኢሳይያስ ከክርስቶስ ልደት ሰባት መቶ ዓመታት በፊት እንዲህ ብሎ ተናገረ ” ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል”።(ኢሳ.9፥6)

ይህን የሰላም አለቃ፤ ዓለም ጠልታ፤ በሀሰት ክስ እና ምስክር ለሞት አሳልፋ ስለሰጠችው፤ አሁን የዓመፅ ዋጋዋን እያገኘች የክህደት ፍሬዋን እየለቀመች ፤ሰላም እርቋት ትገኛለች።

ለእኛ የሰላም ልጆች የዘላለም ንጉሥ የሕዝቡ ሁሉ መድኀኒት የሆነ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፤ የሰላም አለቃ ሆኖ ከተወለደልን 2017 ዓመት ሆኖልናል።

የተወለደው ሕፃን መደኀኒት ነው። አባት ነው። መካር ነው። ኃይልና ብርታት ነው። አምላክ ነው፣ ነጉሥ ነው፣የሰው ብርሃን ነው፣የሰው ሕይወት ነው፣መልካም እረኛ ነው፣ ከሰማይ የወረደ የሕይወት እንጀራ ነው።

የተወለደው ለእኛ ነው። ተሰጥቶናል ተወልዶልናል የሚለው የቅዱሳን ነቢያት አነጋገር የሚያስረዳን ለእኛ እንጂ ለራሱ ወይም ለመላእክት እንዳልተወልደ ነው።

እግዚአብሔር የሰጠን ሰላም ልጁ ነው። እርሱን ቀዳሜ ጸጋ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳለው ቅዱስ ባስልዮስ፤ የሰጦታ ሁሉ መጀመሪያና መጫረሻ፤ ወድ ስጦታ፤ ክቡር ስጦታ፤ታላቅ ስጦታ ብሎ ከመቀበል ውጭ ሌላ ሰላም ከሌላ ሥፍራ አናገኝም።

በእውነት የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሁላችንም ሰላሙን ፍቅሩንና አንድነቱን ስምምነቱን ይስጠን። አሜን!

ክቡራትና ክቡራን የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ!
“””””””””””””””””””””””””””””””””””””””””””””””””””
ሰብአ ሰገል የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? በማለት በኮከቡ እየተመሩ መጥተው ሰግደውለታል።
(ማቴ.2፥1)

ለእግዚአብሔር መንበርከክ፤ ለእግዚአብሔር መገዛት፤ ለሀገር ሰላም ያመጣል፤ ለሀገር ፍቅርን፤አንድነትን፤ ስምምነትን ያመጣል ፣ ከእርሱ የተገኘውን ሥልጣን ገንዘብ ማድረጊያ መንገዱም ይሄው ነው።

ቅዱስ ጳውሎስ ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። ( ሮሜ . 13 ፥ 1) ይላልና የዛሬዎቹ ባለሥልጣናትም የሚያስተዳድሩት ሕዝብ  እንዲመራላቸው፤ እንዲታዘዛቸው፤ እንዲያከብራቸው፤ ሥልጣን ለሰጣቸው የባሕርይ ንጉሥ መገዛት ይገባቸዋል፤ ይህን ካደረጉ የተወለደው ህፃን  የዘላለም አምላክ፤ የሰላም አለቃ ነውና ሰላሙን ያሳድርባቸዋል።

እኛም የሰላም ልጆች በልደቱ እረኞችና መላእክት አንድ ሆነው ” ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ” ብለው እንደዘመሩ የሰላም መዝሙር እየዘመርን፤ የተቸገሩትን እየረዳን፤ የተራቡትን በማብላትና በማጠጣት እንድናከብር አደራ እላለሁ።
ልዑል እግዚአብሔር ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ሰላም ይስጥልን!
መልካም በዓለ ልደት ይሁንልን!