ጥር 23 ቀን 2016 ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””
በማኅበረ ቅዱሳን አስተባባሪነት በዳውሮ ሀ/ስብከት በምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም የተገነባው አዳሪ የአብነት ት/ቤት ጥር 23 ቀን 2016 ዓ.ም የዳውሮና ኮንታ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የአካባቢው ምእመናን በተገኙበት ተመርቋል።
ማኅበረ ቅዱሳን የአብነት ት/ቤት ባልተስፋፋባቸውና የአገልጋይ ካህናትና ዲያቆናት እጥረት ባለባቸው በደቡብ፣በምእራብና በምሥራቅ በሚገኙ አህጉረ ስብከት አብነት ትምህርትን ለማስፋፋት እየሠራ የሚገኝ ሲሆን ይህ የአብነት ት/ቤት ኘሮጀክት አንዱ ነው።
በማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል አስተባባሪነት በአውሮፓ በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ ምእመናን የገንዘብ ድጋፍ የተገነባው የአዳሪ አብነት ት/ቤት 40 ተማሪዎችን በአዳሪነት ፣ 100 ተማሪዎችን በተመላላሽነት ተቀብሎ ማስተማር የሚችል ሲሆን ለት/ቤቱ የሚያስፈልጉ የተለያዩ ቁሳቁሶች የተሟሉለት መሆኑንና ለግንባታውም ከ 3.8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉ ተገልጿል።
በምርቃቱ መርሐግብር ላይ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ መልእክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን የአብነት ት/ቤቱ መገንባት በአገልጋይ እጥረት ምክንያት በሀገረ ስብከቱ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያትን ለማስከፈትና የሚታየውን የአገልጋዮች እጥረት በዘላቂነት ለመፍታት አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ከሁሉም ወረዳዎች ተማሪዎች ተመርጠው እንደሚገቡ በመግለጽ ለኘሮጀክቱ መሳካት ድጋፍ ላደረጉ ምእመናን ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በተያያዘ ዜና ለሀገረ ስብከቱ መንበረ ጵጵስና በታርጫ ከተማ አስተዳደር በተሰጠው ቦታ ላይ ብፁዕነታቸው የመንበረ ጵጵስና ግንባታ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።©m.k