መጋቢት ፫ ቀን ፳፻፲ወ፮ ዓ.ም.
“””””””””””””””””””””””””””””
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ
=============

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በብሔራዊ ምክክር መድረኩ ተሳታፊ እንድትሆንና በአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ውስጥም ተገቢው እውቅና ተሰጥቷት ለአድዋ ድል ያበረከተችውን አስተዋጽኦ የሚያመለክት መታሰቢያ እንዲደረግላት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት አስተዳደር ጉባኤ በዛሬው እለት ባካሔደው መደበኛ ስብሰባው አሳሰበ።

ጉባኤው ቅድስት ቤተክርስቲያን ትምህርት ሚኒስቴር በሌለበት ትምህርት ሚኒስቴር ሆና ብራና ፍቃ ቀለም በጥብጣ በማስተማር ሀገሩንና ቤተ ክርስቲያንን የሚወድና በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ በመፍጠር ያበረከተችው አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ ገብቶ በሃገራዊ ምክክር መድረክ ልትሳተፍ ይገባል ብሏል።

በተያያዘ ዜና ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን በአድዋ ዜሮ ዜሮ ፕሮጄክት ውስጥ በጦርነቱ ድል የነበራትን ከፍተኛ ሚና በሚገልጽ መልኩ ታሪኳ አለመቀመጡ ያሳዘነው መሆኑን የገለጸው ጉባኤው የአድዋ ድል ከብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ትሩፋቱ ባሻገር ሃይማኖታዊ ትሩፋቱ መነገር የሚገባው ታላቅ ድል መሆኑን በመግለጽ በአድዋ ድል ትልቅ ድርሻ ያላት ታላቂቱ ቤተ ክርስቲያን ለድሉ መታሰቢያ በተገነባው ሙዚየም ውስጥ አለመዘከሯ ስህተት ስለሆነ ለሚመለከተው አካል ቅሬታዋን በማቅረብ በሙዚየሙ ውስጥ ተገቢና ትክክለኛ ቦታዋን እንድታገኝ መደረግ እንዳለበት አሳስቧል።

በሌላ በኩል ቤተ እምነቷ እየተቃጠለ፣ አገልጋይ ካህናትና ምዕመናን እየሞቱና እየተሰደዱባት የምትገኘው ቤተ ክርስቲያናች ለሚገጥሟት ችግሮች መፍትሔ እንዳታበጅና በሀገራዊ ምክክር መድረኩ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንዳይኖራት መደረጉ ተገቢ ስላልሆነ ሁለንተናዊ አቅሟን አጠናክራ በየደረጃው በሚደረጉ ሀገራዊ የምክክር መድረኮች ላይ መሳተፍ እንድትችል ከሚመለከተው አካል ጋር ውይይት እንዲደረግ በመወሰን የአስተዳደር ጉባኤው ውሳኔ በመሸኛ ለቋሚ ሲኖዶስ እንዲላክና በቋሚ ሲኖዶስ በሚደረሰው የውሳኔ ሀሳብ መሠረትም ተግባራዊ እንዲሆን ወስኖ የዕለቱን ስብሰባ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ጸሎት አጠናቋል፡፡