በፖላንድ ዋና ከተማ ዋርሶው ከተማ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ የምሥራቅ ጎጃም፣ የጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተባርኮ አገልግሎት ጀምሯል ።
ብፁዕነታቸው ቅዳሜ መጋቢት ፪ ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም በፖላንድ ዋና ከተማ ዋርሶው ቤተ ክርስቲያኑን ባርከው ታቦተ ቅዱስ ገብርኤልን ያስገቡ ሲሆን በማግሥቱ እሑድ መጋቢት ፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም ቅዳሴ ቤቱ በደማቅ መንፈሳዊ አገልግሎት ተከብሯል።
በሀገረ ፖላንድ ኑሮአቸውን መሥርተው ከሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ባሻገር ለድኅረ-ምረቃ ትምህርት የተጓዙ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ኢትዮጵያውያን የቤተክርስቲያናችን ልጆች ቢኖሩም በሀገሪቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አጥቢያ ባለመኖሩ ሲቸገሩና በአገልግሎት ለመካፈል ወደ ሌሎች ሀገራት ለመጓዝ ሲገደዱ አቆይተዋል። በዘንድሮው የጥምቀት በዓልም በአገልግሎት ለመካፈል እና የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የኒውዮርክ እና አካባቢው ሀገረስብከት ሊቀ ጳጳስን ቡራኬ ለመቀበል ከ50 የሚበልጡ የአጥቢያው ምእመናን ወደ ኖርዌይ ኦስሎ ማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተክርስቲያን መጓዛቸው ይታወሳል።
በዚህ ታላቅ ታሪካዊ በዓል ላይ ብፁዕነታቸውን በመከተል መልአከ መዊዕ ልሳነ ወርቅ ውቤ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ መልአከ ጽዮን ቆሞስ አባ ኃይለጊዮርጊስ የሀገረ ስብከቱ ትምህርትና ሥልጠና ክፍል ኃላፊ፤ መልአከ ገነት ቆሞስ አባ አብርሃም የበርሊን ደብረ ገነት ቅዱስ አማኑኤል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ፤ የአጥቢያ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ ወጣት መዘምራን እና ብዙ ምእመናን በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።
እሑድ መጋቢት ፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም በብፁዕነታቸው መሪነት ቅዳሴው ተከናውኖ፣ ቃለ ምዕዳን ተሰጥቶ፤ በመቀጠልም ታቦተ ሕጉ ዑደት አድርጎ በታላቅ መንፈሳዊ ስነ ሥርዓት የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።