በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ እና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ብርሃነ ትንሣኤው የሰላም፣ የሕይወት፣ የጤና፣ የበረከትና የፍቅር ይሆን ዘንድ ተመኝተዋል፡፡

“ሕያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጋላችሁ፣ ተነስቷል እንጂ በዚህ የለም፣ የሰው ልጅ በሐጥያተኞች እጅ ተላልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል፣ በሦስተኛውም ቀን ሊነሳ ግድ ነው እያለ እንደተናገረ አስቡ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን ሞት ይዞ የሚያስቀረው አይደለም ብለዋል፡፡ በሞት ላይ ስልጣን ያለው፣ በሞቱ ሞትን የገደለ፣ በሞቱ ነጻነትን የሰበከ፣ በሲኦል ያሉትን የፈታ ሲኦልን የገለባበጠ፣ ዲያቢሎስን ያሰረ ሕያው ነውም” ብለዋል ብፁዕነታቸው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታላቁን ፆም በፆምና በስግደት ካሳለፈች በኋላ የተቀበለውን መከራ በማሰብ ትንሣኤውን እንደምታከብርም ተናግረዋል፡፡ የክርስቶስ ትንሣኤ የሁላችንም ትንሣኤ ነው ያሉት ብፁዕ አቡነ አብርሃም የክርስቶስ ትንሣኤ ሁላችንን ይገዛ የነበረው ሞት የተሸነፈበት ነውም ብለዋል፡፡

ክርስቶስ ለሰው ልጅ ቸርነቱን ያደረገበት፤ በንጹሕ ደሙ የዋጀበትና የራቀውን ሁሉ ያቀረበበት በመሆኑ ትንሣኤውን በልዩ ሁኔታ እናከብረዋለንም ነው ያሉት፡፡ ከእርሱ ጋር ሳለን ደስታና ሰላም አለን፣ በዓለም ግን መከራ አለ ብለዋል፡፡ የዓለምን ፍላጎትና ምኞት ለማሟላት በተሄደ ቁጥር መከራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።፡፡

አምላክ ዓለምን ያሸነፈበት ጥበቡ እጅግ ድንቅ ነው ያሉት ብፁዕነታቸው የእርሱን ፈለግ የተከተ ሁሉ ዓለምን እና ፈተናዋን ያሸንፋልም ብለዋል፡፡ ክርስቶስ ጦርን በጦር ሳይሆን በፍቅር፣ በሰላም እና በትዕግስት ማሸነፉንም ተናግረዋል፡፡ ክርስቶስ ዓለምን በትዕግስት፣በሰላም በፍቅርና በአንድት እንዳሸነፈ ሁሉ እኛም ሰላም ይኑረን ከዚህ ውጭ ያለው ትርጉም የለውም ነው ያሉት፡፡

ዓለም በጥላቻ ተበክላለች ያሉት ብፁዕነታቸው ብዙዎች በሚያደርጉት አላስፈላጊ ፉክክር ዓለም እየተመሰቃቀለች ንጹሐን እየተጎዱ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ትንሤኤውን የምሥራች የምንባባል ሁሉ ለሰለም ቅድሚያ መስጠት ግድ ይላል ነው ያሉት፡፡ መከራ የበዛባትን ዓለም መሻገር የሚቻለው በመደማመጥ፣ በመቀራረብ እና በመነጋር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጦርና ጦርነት፣ መግደልና መሳደድ ትርጉም እንደሌላቸውም አስረድተዋል፡፡ አላስፈላጊ ውጣ ውረዶች፣ አላስፈላጊ አሸንፍ ባይነት፣ አላስፈላጊ ስምና ዝና ንጹሐንን እየጎዳ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በቂም፣ በበቀል፣ በጥላቻ ወድቀን ትንሣኤውን እናከብራለን ብንል ለምንም አይጠቅመንም ነው ያሉት፡፡ ከሙታነ ሕሊና መራቅ እንደሚገባ ያሳሰቡት ብፁዕ አቡነ አብርሃም ሙታነ ሕሊና ሰላም የጎደላቸው፤ ከጥላቻ ሌላ የማያውቁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ መተዛዘን፣ በጋራ መብላት እና መጠጣት ግድ እንደሚልም ገልጸዋል፡፡

ከመከራው ለመዳን ማሸነፊያ መንገዱን ከእርሱ እንማርም ብለዋል፡፡ ጥላቻና መጥፎ ሃሳብ በምድር ላይ እንዳይነግሥ ፍቅርን ገንዘብ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ መልካም ያደረጉት መልካም ትውልድና መልካም ሀገር ማቆየታቸውንም ገልጸዋል፡፡ በሀገሩ ስደተኛ፣ መጻተኛ፣ ተፈናቃይ፣ በስጋት የሚንከራተት እንዳይኖር እና ሰላም ይበዛ ዘንድ ሕያው የሆነውን አምላክ እንጠይቀው ነው ያሉት ብፁዕነታቸው፡፡

በዓለ ትንሣኤው ሲከበር የታመሙትን በመጎብኘት፣ የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የተቸገሩትን በመርዳት፣ በሰላም እና በፍቅር ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

© ፈለገ ገነት ሚዲያ