ታኅሣሥ ፲፯ ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም
******
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የሚመራ ፲ የልዑካን ቡድን ዓመታዊውን የቅዱስ ገብርኤል በዓል ለማክበር ፣በበዓሉ ላይ ለሚገኙ ምዕመናንን ትምህርተ ወንጌል፣ቃለ በምዕዳንና ቃለ ቡራኬ ለመስጠት ዛሬ ማለዳ ድሬዳዋ ገብተዋል።
የልዑካን ቡድኑም፦
1- ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የዳውሮ ኮንታ ከንባታ ሐላባና ጠምባሮ አህጉረ ስብከት ጳጳስ
2- ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የኢትዮ ሶማሌ ጅግጅጋ ሀገረ ስብከት ጳጳስ
3- ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ የምሥራቅ ጉራጌ ሀገረ ስብከት ጳጳስ
4- ክቡር ንቡረእድ ኤልያስ አብርሃ የመ/ፓጠ/ቤ/ክ መንፈሳዊ ዘርፍ መ/ሥራ አስኪያጅ
5-መ/ሕ ቆሞስ አባ ኃይለገብርኤል ነጋሽ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት ኀላፊ
6- መ/ካ ዕንቈባሕርይ ተከስተ የመ/ፓጠ/ቤ/ክ የካህናት አስተዳደር መምሪያ ኀላፊ
7- መ/ር አካለወልድ ተሰማ (ደ/ር) የመ/ፓጠ/ቤ/ክ አስተዳደር መምሪያ ኀላፊ
8- ሊ/ስ እስክንድር ገ/ክርስቶስ የመ/ፓጠ/ቤ/ክ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኀላፊ
9-ሊቀ ነብያት ሙሴ ኀይሉ የቅዱስ ፓትርያርኩ ፕሮቶኮል ተጠሪእና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተጉዘዋል።
ቅዱስ ፓትርያርኩ እና የልዑካን ቡድኑ ድሬዳዋ አውሮፕላን
ማረፊያ ሲደርሱ በብፁዕ አቡነ በርተሎሚዎስ የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ጳጳስ፣በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ በአቶ ከድር ጁዋርና በካቢኔ አባለቱ፣ በሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች፣ በካህናትና በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች የክብር አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በድሬዳዋ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ለቅዱስነታቸውና ለልዑካን ቡድኑ ደማቅ አቀባበል ያደረጉለት የድሬዳዋ ከንቲባ አቶ ከድር ጅዋር በክብር ዘብ፣በፖሊስ የማርሽ ቡድንና በፈረሰኛ የታጀበ ደማቅና የክብር አቀባበል በማድረግ እንኳን ደህና መጣችሁ፣
እንኳንም አደረሳችሁ ብለዋል።
በመቀጠልም በድሬዳዋ ርእሰ አድባራት ወገዳማት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የእንኳን ደህና መጡ መርሐ ግብር የተካሔደ ሲሆን ብፁዕ አቡነ በርተሎሜዎስ የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።በመልዕክታቸውም የድሬዳዋ ከንቲባ ከኮሪደር ልማቱ ጋር በተያያዘ አብያተክርስቲያናት እንዳይነኩ በማድረግና በልማቱ ሱቃቸው ለፈረሱባቸው አብያተክርስቲያናትም የካሳ ክፍያ በመፈጸም እያደረጉት ላለው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አመስግነዋል።
የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ከድር ጅዋር በበኩላቸው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ በእንግዳ አክባሪነቷ የምትታወቀውና ሁሉም ተቻችሎ የሚኖርባት ከተማችን የቅዱስ ገብርኤል በዓልን ለማክበር የመጡ እንግዶች ሁሉ ተደስተውና ከተማችንን እንደቤታቸው ቆጥረው እንዲቆዩ በማድረግ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድታደርጉ አደራ እላለሁ ብለዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ለልዑካኑ ስለተደረገው አቀባበል አመስግነው የሁሉም ኢትዮጵያዊ ያን ከተማና የአንድነት ተምሳሌት በሆነችው ድሬዳዋ ከተማ አንድነትና ሰላማችሁን፣ፍቅራችሁን፣ ጠብቃችሁና በጸሎት ጸንታችሁ ለመኖር ያብቃችሁ የቅዱስ ገብርኤልን በዓል ለማክበርና ከበረከቱ ለመሳተፍ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የመጣችሁ ልጆቻችን እግዚአብሔር አምላክ በዓሉን በሰላም አሳልፋችሁ ወደየመጣችሁበት በሰላም ይመልሳችሁ ካሉ በኋላ የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ከድር ጅዋር የደግነትና የአንድነት ተምሳሌት መሆናቸውን ሁሉም ስለሚያውቀው ብዙ መናገር አያስፈልገውም ብለዋል።
በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል እየተካሔደ ያለው የኮሪደር ልማት ቤተክርስቲያንን እንዳይነካ ከመንግስት ኃላፊዎች ጋር በመነጋገራችን እስከ አሁን የተነካ ቤተክርስቲያን የለም ያሉት ቅዱስነታቸው በተለይ ደግሞ የድሬዳዋ ከንቲባ የቤተክርስቲያን ድምጽ ሰምተው ወቅታዊና ፈጣን ምላሽ የሚሰጡ ሰለሆነ ምንም አይነት ጉዳት ካለመከሰቱም በላይ የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ተገንዝበናል ካሉ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ለከንቲባ ከድር፣አብረዋቸው ለሚሰሩና ለመላው ቤተሰቦቻቸው ረጅም እጅሜ ከጤና ጋር ይስጥልን በማለት አባታዊ መልዕክታቸውን አጠናቀዋል። በመርሐ ግብሩ ኀላይ ካህናትና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ያሬዳዊ ዝማሬን አቅርበዋል። ሊቃውንትም ቅኔ አበርክተዋል።