መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም
+ + +
በሰሜን ወሎ መንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት ቤተክህነት የወልድያ ከተማ አስተዳደር ቤተክህነት ጽ/ቤት 43ኛ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤውን ትናንት መስከረም 25 ቀን 2017 ዓ.ም በወልድያ መንበረ ንግሥት ኪዳነ ምሕረት የሰንበት ት/ቤት አዳራሽ አካሒዷል።
በብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቡራኬና መሪነት በተካሄደው በዚሁ ጉባኤ የ2016 ዓ.ም የከተማ አስተዳደር ቤተክህነቱ የሥራ ክንውን ሪፖርትና ከቤተ ክርስቲያኗ የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ የተቀዳ መንፈሳዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የ2017 ዓ.ም ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
ስብከተ ወንጌልን በማጠናከር፣ ገዳማትና አድባራት የራስ አገዝ ልማትን በማስፋፋትና ሰንበት ትቤቶችን በማጠናከር አበረታች ሥራዎች መከናወናቸውን የወረዳ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበባት አክሊለ ብርሃን ተመስገን ባቀረቡት ሪፖርት አመላክዋል፡፡
የመረጃ ምንነት፣ አስፈላጊነትና አደረጃጀትን አስመልክቶ በሀገረ ስብከቱ የዳታቤዝ ባለሙያ ገለጻ የተደረገ ሲሆን የቤተክርስቲያኗን አጠቃላይ መረጃዎች አደራጅቶ ለመያዝ ታስቦ የተዘጋጀ ቅጽ ላይም ማብራሪያ ተሰጥቷል። የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ፍሥሐ ጌታነህ በመሪ እቅድ ትግበራ፣ በሰንበት ትምህርት ቤቶች መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ታስቦ የተዘጋጀው ሥርዓተ ትምህርት አተገባበር፣ ብልሹ አሠራርን መቀነስና በአገልጋይነት መንፈስ መሥራት እንዲሁም መልካም አስተዳደር ማሻሻልን አስመልክተው መልእክት አስተላልፈዋል።
ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቃለ ምዕዳንና የሥራ መመሪያ የሰጡ ሲሆን ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ያሏቸውን አገልጋዮችና ተገልጋዮች ልማድን አስወግደው ለምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣ በቤተክርስቲያን የሚስተዋሉ ብልሹ አሠራሮችን ለማስቀረት የቤተክርስቲያኗን መሪ እቅድ በአግባቡ እንዲተገበር፣ የልኅቀት ማእከላትን በማስፋፋት ተተኪ ሊቃውንትንና መነኮሳትን ለማፍራት በትኩረት እንሠራለን ብለዋል።
ቤተክርስቲያን በመንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዋ ተጨባጭ ለውጥ እንድታስመዘግብ መሪ እቅዱን በቁርጠኝነት መተግበር ይገባል ያሉት ብፁዕነታቸው የአብነት ትምህርት ቤቶችና የሰንበት ትምህርት ቤቶችን በማጠናከር ተተኪ ሊቃውንትንና ምእመናንን ለማፍራት ኹሉም የድርሻውን እንዲወጣ አባታዊ መመሪያ አስተላልፈዋል።
በቤተክርስቲያን ለውጥና እድገት እንዲመጣ በመሻት ምእመናን የሚሰጡትን ሀሳብ ኸሉም በተሠማራበት በቅንነት ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል። በጉባኤው ብፁዕነታቸውን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የወልድያ ከተማ አስተዳደር ቤተ ክህነትና የጉባላፍቶ ወረዳ ቤተ ክህነት ኀላፊዎች፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎችና የሰበካ ጉባኤ አባላት ፣ የሰንበት ትምህርት ቤትና የማኅበረ ቅዱሳን ወልድያ ማእከል ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በተጠናቀቀው የአገልግሎት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ሰበካ ጉባኤያት፣ ተቋማትና ግለሰቦች የዕውቅና ሽልማት ተሰጥቷል።
መረጃው የሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ነው