የካቲት ፴ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””””””
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ
***

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ በቦረና በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ የማሰባሰብ እንቅስቃሴን የሚያስተባብር በብፁዕ አቡነ አቡነ ማርቆስ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ሰብሳቢነትና በሊቀ ትጉሃን እስክንድር ገብረ ክርስቶስ የጠቅላይ ቤተክህነት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ጸሐፊነት የሚመራ ዐቢይ ኮሚት አቋቁሟል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ የካቲት ፳ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም ባደረገው ሠደበኛ ስብሰባ በሦስት ብፁዓን አባቶች እና በሁለት የጠቅላይ ቤተክህነት የሥራ ኃላፊዎች የሚመራ ዐቢይ ኮሚቴ እንዲዋቀርና ወደ ሥራ እንዲገባ ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ውሳኔውን እንዲያስፈጽም ኃላፊነት ሰጥቷል።

በዚህም መሠረት ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በክልል ትግራይ ደቡባዊ ዞን ማይጨው፣ የደቡባዊ ምሥራቅ ትግራይ አህጉረ ስብከት፣የቅርስ ጥበቃና ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያና የማኅበራት ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን የጠቅላይ ቤተክህነት ም/ዋና ሥራ አስኪያጅና ሊቀ ትጉሃን እስክንድር ገብረ ክርስቶስ የጠቅላይ ቤተክህነት ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ የድጋፍ ማሰባሰቡን ሥራ እንዲያስተባብሩ በቋሚ ሲኖዶስ መመረጣቸውን በመጥቀስ ለተቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴ በጻፈው ደብዳቤ ድርቁ በተከሰተበት ቦታ በመገኘትና በድርቁ የደረሰውን ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት ዕርዳታውን እንዲያሰባስቡና ለተጎጂዎች እንዲያደርሱ አሳስቧል።

ይህንን ተከትሎ ዐቢይ ኮሚቴው በቅርቡ ስብሰባ በማድረግ የተጣለበትን ከባድ ኃላፊነት ለማስፈጸም የሚያስችለውን እቅድ በማውጣት ወደ ተግባር የሚገባ መሆኑ ታውቋል።