የካቲት ፲፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ

በጥንታዊውና ታሪካዊ ዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም በተፈፀመው ጥቃትና የመነኮሳት ግድያን አስመልክቶ በምሥራቅ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ክቡር አቶ አባቡ ዋቆ የተመራ ውይይት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፡ የምሥራቅ ሸዋ ዞን የጸጥታ ክፍል ከፍተኛ ኃላፊዎች ፡ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ም/ሥራ አስኪያጅ በሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮነን የተመራ ልዑክ ፡ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤና የሀገረ ስብከቱ ልዑካን ፡ የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አበምኔትና የገዳሙ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

በደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በግፍ የሰማዕትነትን ጽዋ የተቀበሉ አባቶች መርዶ በትናንትናው ዕለት የተሰማ ሲሆን በመላው ዓለም የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ሀዘናቸውን በመሪር እንባ እየገለጹ ይገኛሉ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከትም ከገዳሙ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በትኩረት ጉዳዩን ሲከታተል የቆየ ሲሆን በዛሬ ዕለትም በቢሾፍቱ ከተማ የኢ/ፌ/ዴ/ሪ አየር ኃይል ግቢ አራት ሰዓታትን የፈጀ ሰፊ ውይይት ሲደረግ ቆይቷል፡፡

በውይይቱ የተቀመጡ የመፍትሔ ሃሳቦች፡-

1ኛ፡- በመንግሥት የፀጥታ አካላት አማካኝነት የሰማዕታቱን አስክሬን ከወደቁበት አንስቶ በክብር ወደ ገዳሙ በማምጣት ሥርዓተ ቀብር እንዲፈፀምላቸው

2ኛ- በቋሚነት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሀገር መከላከያ ሠራዊትና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጸጥታ መዋቅር ገዳሙንና ገዳማውያንን በዘላቂነት መጠበቅ እንዲቻል

3ኛ፡- በመንግሥትና በሀገረ ስብከቱ እንዲሁም በቤተክርስቲያን አባቶች ልባቸው የተሠበረና የተጎዱ የገዳሙ አባቶችና እናቶችን በጋራ ማጽናናት እንዲችል፡፡ የውይይቱ የውሳኔ ሃሳቦች ሲሆን ይኼው ግብረ ኃይል ከሀዘኑ በኋላ ዳግም ተገናኝቶ በተሠሩ ሥራዎችና ወደ ፊት አስተማማኝ ሰላም በሚሠፍንበት ጉዳይ ላይ ለመመካከር ቀጠሮ ተይዞ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የዕለቱ ውይይት በጸሎት ተዘግቷል፡፡

© የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሐመረ ተዋሕዶ ሚዲያ