መስከረም ፳፫ቀን ፳፻፲ ወ፮ዓ.ም
“””””””””””””””””””””””””””””””
የአሀት ኦርቶዶክሳውያን አብያተክርስቲያናት ብፁዓን አባቶች ጉባኤ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኋላ የመጀመሪያ የሆነውን የጋራ የጸሎተ ቅዳሴ አገልግሎት መስከረም ፲፪ ቀን ፳፻፲፮ ዓ/ም በዌስት ኦሬንጅ ኒውጀርሲ በሚገኘው ደብረ ገነት ቅዱስ አማኑኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አከናውነዋል።
የጉባኤው አባላት በሆኑ ብፁዓን አባቶች ውሳኔ መሠረት የዘንድሮው ሥርዓተ ቅዳሴ እንዲመራ የታሰበው በብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቢሆንም ብፁዕነታቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በነበረባቸው ተደራራቢ ሥራ ምክንያት መገኘት ባለመቻላቸው በብፁዕነታቸው የተወከሉት መምህር አረጋዊ ሥርዓተ ቅዳሴውን በመምራት ተገቢውን መንፈሳዊ አገልግሎት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቀኖና መሠረት ተሰጥተዋል።
በሥርዓተ ቅዳሴው ላይም ከግብፅ፣ ከሕንድ፣ ከሶርያ፣ ከአርመንያና ከኤርትራ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የመጡ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናትና ምእመናን ተገኝተዋል። ከቅዳሴው ባሻገርም በመጋቢት ወር ፳፻፲፭ ዓ/ም በጳጳሳት ጉባኤ በተወሰነው መሠረት አንድነትን ለማጠናከር በሚረዱ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይት ተደርጓል።
ይህ የጳጳሳት ጉባኤ የሚያሳልፋቸው ጠቃሚ መንፈሳዊ ውሳኔዎች በሁሉም አሀት ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት ተፈጻሚ እንዲሆኑ በብዙዎቹ አብያተ ክርቲያናት የታመነበት ሲሆን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም የቅዱስ ሲኖዶስን የምልአተ ጉባኤ ውሳኔን እየጠበቀ መሆኑ ተገልጿል።
በጉባኤው ፍጻሜ ላይም የደብረ ገነት ቅዱስ አማኑኤል ቤተክርስቲያን ካህናትና ምእመናን በኢትዮጵያ ባሕላዊ ምግብና መስተንግዶ እንግዶችን አክብረዋል።
የአሀት ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤውን በብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በአብያተ ክሮስቲያናትና በውጪ ግንኙነት ኀላፊነት እየመሩ ይገኛሉ።