በአርሲ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች በኦርቶዶክሳውያን ላይ የተፈጸመውን ግድያ የጠቅላይ ቤተክህነት አስተዳደር ጉባኤ አወገዘ።

ኅዳር ፳፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ዓ.ም
“””””””””””””””””””””””””””
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ
******
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት አስተዳደር ጉባኤ በዛሬው እለት ባደረገው መደበኛ ስብሰባ በምሥራቅ አርሲ አንዳንድ ወረዳዎች በኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችን ላይ የደረሰውን የሞት አደጋ በተመለከተ ኅዳር 24 ቀን 2016ዓ.ም ከሀገረ ስብከቱ በስልክና በደብዳቤ የደረሰውን መረጃ መነሻ በማድረግ ውይይት ካደረገ በኋላ ውሳኔ አስተላልፏል።

ሀገረ ስብከቱ ለጠቅላይ ቤተክህነት ባደረሰው መረጃ በአርሲ ዞን በሹርካ ወረዳ ሶሌ ሚካኤል፣በዲገሎ ማርያም፣ በሮቤ እንደቶ ደብረ ምጥማቅ ማርያም አብያተክርስቲያናት ላይ በተለያዩ ጊዜያት 36 ኦርቶዶክሳዊያን በደረሰባቸው ጥቃት ሕይወታቸውን ማጣታቸውን በሪፖርቱ አሳውቋል።

በተጨማሪም በሶሌ ዲገሉ እና ጢጆ ለቡ በተባሉ ቀበሌዎች 28 ኦርቶዶክሳዊያን ከየቤታቸው ተለቅመው የተገደሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም 7ቱ ሴቶችና 21ዱ ወንዶች መሆናቸው ነተገለጸ ሲሆን በዚህ ጥቃትም እድሜያቸው ከሰባ ዓመት አዛውንት እስከ ሃያ ስምንት ቀን ጨቅላ ሕጻናት የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸው ተገሌጿል።

ከሁለት ቀናት በፊትም በዲገሉ ማርያም ቤተክርስቲያን 5 ኦርቶዶክሳዊያን ከመገደላቸው በተጨማሪ የሦስት ኦርቶዶክሳውያን ቤት መቃጠሉ ታውቋል።በተያያዘም ከዚህ ቀደም በሮቤ አንዲቶ ደብረ ምጥማቅ ማርያም ቤተክርስቲያን በዓለ ማርያምን አክብረው ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ የነበሩ ሦስት ኦርቶዶክሳዊያን ጨለማን ተገን ባደረጉ ነፍሰ ገዳዮች መገደላቸውንም ሀገረ ስብከቱ በላከው በሪፖርት ገልጿል።በማያያዝም በመንግሥት በኩል አጥፊዎች ላይ እርምጃ መወሰድ የተጀመረ መሆኑንም ሀገረ ስብከቱ ገልጿል።

አስተዳደር ጉባኤው በምሦራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት አንዳንድ ወረዳዎች በኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችን ላይ በደረሰው ጥቃትና ሞት በእጅጉ ማዘኑን ገልጾ በዚህ መልኩ በኦርቶዶክሳዊያን ወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው ጥቃትና ሞት አሳዛኝና ድርጊቱም በጽኑ የሚኮነንና የሚወገዝ ተግባር ነው በማለት አውግዞታል።

ይህን የመሰለ በጭካኔ የተሞላ ድርጊትም መቆም የሚችልበት፣ወገኖቻችን ሕገ መንግስታዊ ከለላን በማግኘት በሰላም መኖር የሚችሉበት መንገድ መፈጠር አለበት ያለው አስተዳደር ጉባኤው በጉዳዩ ዙሪያ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ ጉዳዩ ከፍ ባለ ደረጃ መታየት የሚገባው መሆኑን በማመን ለቋሚ ሲኖዶስ ቀርቦ ውሳኔ ማግኘት ይችል ዘንድ ለቋሚ ሲኖዶስ ግብዓት የሚሆን ምክረ ሐሳብን አቅርቧል።

አስተዳደር ጉባኤው በተለያዩ ቦታዎች የሚከሰቱ ችግሮችን ተከትሎ አህጉረ ስብከት ለጠቅላይ ቤተክህነቱ ሪፖርት ባደረጉ ጊዜ ጉዳዩን በማየት ውሳኔ የሚያስተላልፍ መሆኑን ገልጾ ሪፖርት ባልተደረገበትና በሚዲያዎች የተነገሩ መልዕክቶችን ብቻ መነሻ በማድረግ ውሳኔ ማስተላለፍ በተቋም ደረጃ ቤተክርስቲያንን የሚጎዳ ስለሆነ አህጉረ ስብከት ችግሮች በገጠሟቸው ጊዜ ሁሉ በፍጥነት ሪፖርት
መላክ ይገባቸዋል ብሏል።