ሰኔ ፳፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም
“”””””””””””””””””””””
አዲስ አበባ -ኢትዮጵያ
==============
በግንቦት ፳፻፲፭ ዓ/ም ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የጸደቀውንና ለቤተክርስቲያናችን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት መሳለጥ ተጨባጭ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የታመነበትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መሪ እቅድ በሠፊው የሚተነትንና የሚያስረዳ የአንድ ቀን ሥልጠና የመንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት አስፈፃሚ አካላት ለሆኑት ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ የመምሪያና ድርጅት ኃላፊዎችና ለምክትል ኃላፊዎች ተሰጠ።
በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽርሐ-ተዋሕዶ አዳራሽ የተሰጠው ሥልጠና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፖትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ጸሎት እና አባታዊ መመሪያ የተከፈተ ሲሆን ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የኒው ዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በቅዱስ ሲኖዶስ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መሪ እቅድ ዓቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን የመንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ምክትል ሥራ አሥኪያጅ በመክፈቻው መርሐ ግብር ላይ ታድመዋል።
ቅዱስነታቸው በመክፈቻው ሥነሥርዓት ላይ ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት “ይህ መሪ እቅድ ቤተክርስቲያናችንን የሚጠቅም የቤተክርስቲያናችንን መንፈሳዊ አገልግሎት የሚያሳድግ ነው። ይህ መሪ እቅድ ተግባራዊ ከሆም ሥራዎች በአግባቡ ስለሚሠሩ የሚያማና የሚታማ ስለማይኖር ሁሉም አገልጋይ ለተግባራዊነቱ በቅንነትና በታማኝነት መረባረብ ይኖርበታል” ብለዋል።
ብፁዕ አቡነ አብርሃም በበኩላቸው ባደረጉት የመግቢያ ንግግር የመሪ ዕቅድ ዝግጅቱ ከ፰ ዓመታት በላይ መውሰዱንና ዛሬ ለመምሪያና ለድርጅት ኃላፊዎችና ምክትል ኃላፊዎች ግንዛቤ በመሥጠት የተጀመረው የገለጻ መርሐ ግብር እስከ ወርኃ ጥቅምት ቀጥሎ እስከ አህጉረ ስብከት ላሉ የሥራ ኃላፊዎች እንደሚቀጥልና ከጥቅምት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በኋላ ወደ ሥራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናው በመሪ እቅዱ ላይ የተያዙ ሦስት (መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ) ዓበይት ዘርፎች ላይ አትኩሮት አድርጎ ተሰጥቷል።
የመጀመሪያውና የመንፈሳዊ ልማት ዘርፍ ላይ ያተኮረው ሥልጠና የመሪ ዕቅድ ትግበራ ዓቢይ ኮሚቴ አባል በሆኑት በዶ/ር በለጠ ብርሀኑ የተሰጠ ሲሆን ልማትና ኢኮኖሚ ላይ ያተኮሩት የመሪ ዕቅዱ ክፍል ደግሞ በዶ/ር ሰሎሞን ፀሐዬ ቀርቧል።
መርሐ ግብሩን ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ በመንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የመሪ እቅድ ትግበራ መምሪያ ዋና ኃላፊ የመሩት ሲሆን የሥልጠናውን ሂደት በማሳለጥና ውይይቶችን በመምራት ረገድ የኮሚቴው አባል ሊቀ ትጉሃን በድሉ አሰፋ ሰፊ አገልግሎት ተሰጥተዋል።