ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም.
+ + +
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት የሕግ አገልግሎት መምሪያ ሥር የተቋቋመው የሕግ ባለሙያዎች ዐቢይ ኮሚቴ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ለቅድስት ቤተክርስቲያን ሕግ ተኮር የሆኑ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ የቆየ መሆኑን ተገልጿል።
ጉባኤው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕዳርና የሰሜን ጎጃም እህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የየመሪያ ኀላፊዎች ፣ የሕግ ባለሙያዎች ዐቢይ ኮሚቴ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው የሕግ ባለሙያዎች በተገኙበት ተካሂዷል።
ጉባኤው በሕግ አገልግሎት መምሪያ ኀላፊው አፈ መምህር አባ ገብረ ሥላሴ (ቆሞስ) የተመራ ሲሆን ጠበቃ አያሌው ቢታኔ የአፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል። በሪፖርቱም የሕግ ባለሙያዎች በቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪ ተደርጎላቸው ሥራ ከጀመሩበት ከጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለቤተክርስቲያን ዘርፈ ብዙ የሙያ አገልግሎት እየሰጠ የቆየ መሆኑ ተገልጿል።
ይህ የባለሙያዎች ዐቢይ ኮሚቴ ለቤተክርስቲያን ሲሰጣቸው ከነበረውና ወደፊትም የሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል የችሎት ክርክርና የምክር አገልግሎት ፣ የሕግ ማርቀቅና የሰነድ ዝግጅት፣ የሕግ ጥናት፣ ምርምርና ስልጠና፣ የመረጃ መሰብሰብ ፣ ማጠናቀርና መተንተን ፣ የንቃተ ሕግ ግንዛቤ መፍጠር እና የመሳሰሉትን አገልግሎቶች እንደሆነ ተገልጿል።
በጉባኤው ላይ የተገኙት ነባርና አዳዲስ ባለሙያዎች ለአገልግሎቱ መሳካት ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚያደርጉ በመግለጽ የአባልነት ፎርም ያልሞሉ አባላትም በተዘጋጀው የአባልነት መሙያ ሰንጠረዥ ላይ ሞልተዋል ።
ከአፈጻጸም ሪፖርቱ በመቀጠል ወደፊት ከአህጉረ ስብከት ጋር በሚካሄደው ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ላይ አቅጣጫ የሚያሳይ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቧል። በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ መሠረት ዐቢይ ኮሚቴው በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር ወደ ሀገረ ስብከቶች እንዴት ማውረድ እንደሚቻል አቅጣጫ ሰጥቷል።
በመጨረሻም ጥሩ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ጠበቆች በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክልነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣በባሕርዳር እና ሰሜን ጎጃም አሕጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቡራኬ የምስጋናና የምስክር ወረቀት ተሰጥቶ በምዕራብ ጎንደር ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ሰላማ ጸሎት ተደርጎ የጉባኤው ፍጻሜ ሆኗል።