አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
***
ጥቅምት ፳፯ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ዓ.ም
“””””””””””””””””””””””””””””””
በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በኩል በ2016 ዓ/ም ሊሠሩ በታቀዱ ቀጣይ የሥራ ተግባራት ረቂቅ ጽሑፍ ላይ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ እስከ ክፍላተ ከተማ ከሚገኙ የወንጌል መምህራን ጋር ለአንድ ቀን የቆየ ሥልጠናና ውይይት አካሂዷል።
በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 44ንዑስ ቁጥር 4ላይ ከተዘረዘሩት የአስፈጸሚነትና የአስተዳደር ሥራዎችን ከሚመሩ 18መምሪያዎች አንዱ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ነው።
የቤተ ክርስቲያንም ዋና ተልእኮዋ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት ምእመናንን ለእግዚአብሔር መንግሥት ማብቃት ነው።
ሌሎቹ መምሪያዎችም ዋና ተልእኳቸው ለስብከተ ወንጌል ድጋፍ መስጠትና ረዳት ሆነው ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት ነው።
በመሆኑም መምሪያው ይህንን ተልእኮ አጠናክሮ ለመቀጠል ካቀዳቸው ቀጣይ የሥራ ተግባራት መካከል የሥምሪት፣የሥልጠና፣የሚድያ እና የሥነ ጽሑፍ ክፍሎችን በማዋቀር ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ድረስ ባሉት መዋቅሮች ሰባክያነ ወንጌልን በማሠማራት ለምእመናን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት መስጠት በመሆኑ ይህንኑ ተግባር አጠናክሮ ለመሥራት ይረዳ ዘንድ ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ/ም ቦሌ በሚገኘው የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ሕንጻ ከመምሪያው ጀምሮ እስከ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ድረስ የሚገኙትን የወንጌል መምህራን በማሰባሰብ ለአንድ ሙሉ ቀን የቆየ ስብከተ ወንጌል ተኮር ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን በተጨማሪም በመምሪያው በኩል በ2016 ዓ/ም ሊሠሩ በታቀዱት ቀጣይ የሥራ ተግባራትን አስመልክቶ ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዷል።
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በሰጡት አባታዊ አስተያየት ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌልን የማስፋፋት ተቀዳሚ ሥራዋ ሲሆን ዋና ግቡና ዓላማው ምእመናንን ለእግዚአብሔር መንግሥት ማብቃት ነው ያሉ ሲሆን ይሁን እንጂ ወንጌል ከጥቅም ጋር አብሮ ሊሄድ የማይችል ስለሆነ ሕይወት የሚሰጠውን ወንጌል ከጥቅም ጋራ ከተያያዘ ውጤታማ ለመሆን ያዳግታል ብለዋል።
ብፁዕነታቸው አያይዘው እንደገለጹት አገልጋዮች ደመወዝ እንደሚያስፈልጋቸው ቢታወቅም አገልግሎታቸው ግን ከሚያገኙት ጥቅም በላይ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ብፁዕነታቸው ጨምረው እንደገለጹት የወንጌል መምህራን ጥቅማጥቅምን በመፈለግ ወንጌል ለመስበክ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ልውጥ ለማምጣት አዳጋች ይሆናል ብለዋል።
መልአከ ሰላም ዶክተር አባ ቃለጽድቅ ሙሉጌታ
የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ዋና ሐላፊ በበኩላቸው እንደገለጹት ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ጥረት በምናደርግበት ጊዜ ሁሉ በርካታ ፈተናዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ።
ሆኖም ፈተናዎቹን እየተቋቋምን ለአስር ዓመታት በተዘጋጀው መሪ ዕቅድ መሠረት ተግተን እንሠራለን ብለዋል።
ውይይቱም ሆነ ሥልጠናው ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ድረስ አጠናክረን እንቀጥላለን ያሉት የመምሪያው ሐላፊ ለሥራው መነሣሣት ምክንያት የሆነው ቀደም ሲል አባቶቻችን ያደራጁትን መዋቅር እንደገና ወደቀድሞው አሠራር በመመለስ አጠናክረን ለመቀጠል ነው ብለዋል።የውይይቱና የሥልጠናው ተሳታፊዎችም በበኩላቸው እንደገለጹት በመምሪያው ተዘጋጅቶ የቀረበው ቀጣይ የሥራ ተግባራት ዕቅድ ችግሮችን የሚያስወግድ የ ቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ የሚያፋጥን ስብከተ ወንጌልን የሚያጠናክር በመሆኑ በቋንቋዎች ጨምር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል ብለዋል።