የካቲት ፲ ቀን ፳፻፲ወ፮ ዓ/ም አዲስ አበባ
ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ የምሥራቅ ጎጃም፣ የጀርመንና አካባቢው አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለአራት ደቀ መዛሙርት ሥልጣነ ክህነትን ሰጡ !
ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ የምሥራቅ ጎጃም፣ የጀርመንና አካባቢው አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ ማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን በመገኘት ክህነቱ በተሰጠበት መቅደስና በመላዋ ኖርዌይ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ለሚያገለግሉ አራት ደቀ መዛሙርት የዲቁና ሥልጣነ ክህነት ሰጥተዋል።
በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ኤልያስ መልካም ፈቃድ አሳሳቢነት የአብነት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ለቆዩት አራት ደቀ መዛሙርት የዲቁና ሥልጣነ ክህነት በሰጡበት ወቅት ለአገልጋዮቹ በሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ትምህርት አስተምረው በዓለም ዙሪያ ያለችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በቅንነትና በእውቀት እንዲያገለግሏትም አባታዊ መመሪያም አስተላልፈዋል።
የኦስሎ ማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ተተኪ ካህናትን ለማፍራትና ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ለማብቃት የፊት ለፊትና የበይነ መረብ መርሐ ግብሮችን በማዘጋጀት ተተኪ የአብነት ትምህርቶችን በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ከደብሩ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።