ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምህረትከ ወይጸግቡ ጠላተ ገዳም(በቸርነትህ ዓመታትን ታቀዳጃለህ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል) መዝ 65:-11

መስከረም 1/2017 ዓ.ም
_______
የከሚሴ ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና በሆነው በከሚሴ ከተማ ውስጥ ሁለት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ያሉ ሲሆን ሁለቱም በአንድ ሰበካ ጉባኤ የሚተዳደሩ ናቸው።
የ2017 ዓ.ም አዲስ ዓመት በዚሁ እለት ሲከበር የመጀመሪያውን ከፍለ ጊዜ በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት የሀይቅ እስጢፋኖስ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መ/ር የሆኑት መ/ር አምደ ብርሀን የ2017 ዓመተ ምህረት በዓላትና አጽዋማት የባሕረ ሀሳብ ቀመር አውርደዋል።

በሁለተኛው ክፍለ ጊዜ የአጥቢያዎች ወረዳ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል ክፍል ሃላፊ መ/ር ኤፍሬም መላኩ “ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምህረትከ ወይጸግቡ ጠላተ ገዳም” ። መዝ 65:-11 የቅዱስ ዳዊትን የምስጋና ሃይለ ቃል መነሻ አድርገው እግዚአብሔር አምላክ በቸርነቱ እለታትን ሳምንታትን ወርሀትንና ዐመታትን ሳያጎድል ሳይረሳ በየዓመቱ ለሰው ልጅ ይሰጣል/ያድላል በማለት ትመህርተ ወንጌል ሰጥተዋል።

በዚህ አዲስ ዓመት ሁላችንም የቆየ ቂምን ጥልን በመተው ንጹህ ሁነን ሥጋ ወደሙ ተቀብለን አዲስ ህይዎት ልንኖር ይገባልም ብለዋል። እኛ ኢትዮጵያውያን መስከረምን አዲስ ዓመት ብለን የምናከብረው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ :-መንግሰተ ሰማያት ቀርባለችና ንሥሐ ግቡ ጥርጊያውንም አሳምሩ እያለ ያስተማረበት ወር ሰለሆነ እና የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ምትረተ ርእሱን መታሰቢያ በማድረግ ነው ብለዋል ።

ከሁለተኛው የትምሀርት ክፍለ ጊዜ በመቀጠል ታቦተ ህጉ ሦስት ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑን ከዞረ በኋላ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ዓመት ለባርኮ ባርኮ ዐውደ ዓመት: ንዒ ማርያም ለምሕረት ወሳህል (ዐውደ ዓመትን ለመባረክ ለይቅርታና ለምህረት ማርያም ነይ የሚወለውን ወረብ አቅርበዋል)።
በመቀጠልም የደበሩ ሰንበት ትምህርት ቤት “ሰመዮ ብርሀነ በውስተ ጽልመት ለዘተወልደ እምብእሲት ተወልደ እምብእሲት : አእሚሮ ዮሐንስ እምከርሰ እሙ ሰገደ ወልደ መካን ለወልደ ድንግል
(ከሴት የተወለደው ብርሀንን በጨለማ ውስጥ ሾመው። የመካኒቱ ልጅ ዮሐንስ ለድንግል ልጅ አውቆ በእናቱ ማህጸን ውስጥ ሰገደ) የሚለውን ወረብ ካቀረቡ በኋላ የሀገረ ስብከቱ ዋና ስራ አስኪያጅ መልአከ ገነት ደጀን ተስፋዬ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አቅርበው በቃለ ምእዳን የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።

መስከረም 1/2017 ዓ.ም
መረጃውን ያደረሰን ሀገረ ስብከቱ ህዝብ ግንኙነት ክፍል ነው።