በክልል ትግራይ ካሉ ብፁዓን አባቶች ጋር የተፈጠረውን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት እየተሠራ እንደሆነ የሰላም ልዑኩ ገለጸ ።
ሰኔ ፯ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም
*****
አዲስ አበባ -ኢትዮጵያ
“””””””””””””””””””””
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይነበባል
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ አሜን !!!
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና የስምምነት ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የካቲት 7 ቀን 2015 ዓ.ም በቅዱስነታቸው ፊርማ ባወጣው ደብዳቤ በትግራይ ክልል የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ በካህናት ፣ በምእመናን ፣ በገዳማትና በአድባራት ላይ ስለደረሰው ጉዳት የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን በይፋ መግለጹ ይታወሳል።
በግንቦት ወር ባካሄደው የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤም በክልል ትግራይ የሚገኙ አባቶቻችን የሚያነሱትን ቅሬታ በተመለከተ ጉዳዩ በውይይትና በህግ የሚፈታበት መንገድ እንዲፈጠር ቀደም ሲል በቅዱስ ሲኖዶስ የተሰየመው ኮሚቴ ሥራውን እንዲቀጥል መመሪያ ሰጥቶ ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ውሳኔ አስተላልፏል።
የተቋቋመው ኮሚቴም ችግሩ በሰላማዊ መንገድና በስምምነት መቋጨት የሚችልበትን አቅጣጫ በመቀየስ በርካታ የቅድመ ውይይት ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።ወደፊትም የቅዱስ ሲኖዶስን መመሪያ በመቀበል ችግሩ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በተከተለ አግባብ መፍትሔ እንዲያገኝ ለማድረግ የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ ደፋ ቀና እያለ ይገኛል።
በክልል ትግራይ የሚገኙ ብፁዓን አባቶቻችን የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ሁሉ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በተከተለ አግባብ ለመፍታት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን የምታደርገውን የእናትነት እንቅስቃሴ በማዛባት ልዩነት እንዲሰፋና የቤተክርስቲያናችን ተቋማዊ አንድነት እንዲናጋ ሌት ተቀን የሚጥሩ አንዳንድ የሚዲያ ተቋማትም ችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሔ እንዳያገኝ ሆን ብለው እየሠሩ እንደሚገኙ እንገነዘባለን።
ይሁንና ችግሩ የሚፈታው በእልህና በቁጣ ልዩነትን በማስፋትና በመራራቅ ሳይሆን በሰከነ መንገድ በሰለጠነ አስተሳሰብና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን መሠረት ባደረገ በግልጽ ውይይት መሆኑን በመገንዘብ የችግሩ መነሻዎችን አሁን ያሉበትን ደረጃና ወደፊት ሊደረግ የሚገባ የሚባሉ ነጥቦችን በመለየት በውይይት መፍታትና በመጨረሻ ጉዳዩን በእርቀ ሰላም ማጠቃለል እንደሚገባም ኮሚቴው በጽኑ ያምናል።
ስለሆነም በክልል ትግራይ የሚገኙ ብፁዓን አባቶቻችን ቀደምት አባቶቻችን ለሃይማኖታቸው አንድነትና መስፋፋት እንዲሁም ለቀኖና ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ የከፈሉትን መስዋዕትነት መሠረት በማድረግ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችሁ አንድነትና ሉዓላዊነት በጽናት በመቆም ተፈጠሩ የሚባሉ ችግሮችን ሁሉ በዝርዝር ለማቅረብ ለውይይት ዝግጁ እንድትሆኑ መልእክታችንን እያስተላለፍን የምታቀርቧቸውን የውይይት ነጥቦች መሠረት በማድረግ ችግሮቹን በስምምነት ለመፍታት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ዝግጁ መሆኗን እንወዳለን።
በዚህም የውይይትና የሰላም መልእክታችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ያስተላለፈችውን ጥሪ በመቀበል በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውይይትና ለስምምነት ዝግጁ እንድትሆኑ ጥሪያችንን እያስተላለፍን በቅርብ ቀናት ውስጥ የሰላም ልዑኩ ለውይይት ወደ ክልል ትግራይ መቀሌ ከተማ ስለሚጓዝ በጋራ በምናደርጋቸው ቦታና ጊዜ የውይይትና የስምምነት ጉባኤ የሚደረግ ይሆናል።
የፌዴራል መንግሥትና የክልል ትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርም ችግሩ በሰላማዊ መንገድና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በጠበቀ መልኩ መፍትሔ ያገኝ ዘንድ የሚደረገውን ጥረት ሁሉ በመደገፍና ለውይይቱ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግልን በዚሁ አጋጣሚ መልእክታችንን ለማስተላለፍ እንወዳለን።
አምላካችን እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ሀገራችንንና ሕዝባችንን ይባርክ !
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የሰላምና የስምምነት ኮሚቴ
ሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ