በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በኮቸሬ ገደብና ጮርሶ ወረዳ ቤተክህነት የሰንበት ት/ቤት አንድነት ተመሠረተ!!
የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ ሊቀትጉሃን ቀሲስ ሀብታሙ አበበ  ከፊት ይልቅ ትጉ!! በ፪ኛ ጴጥ ፪:፲ ያለውን አምላካዊ ቃል መነሻ በማድረግ የሰንበት ት/ቤት አባላት መጠራታቸውን መመረጣቸውን በመመልከት ከበፊት ይልቅ መትጋትና የቅድስት ቤተክርስቲያን ሥርዓት በመጠበቅና በማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በሰፊው አስተምረዋል።

የኮቸሬ ገደብና ጮርሶ ወረዳ ቤተክህነት ዋና ፀሐፊ በኩረ ትጉሃን ቀሲስ አስቻለሁ ገ/መድኀን በመርሐ ግብሩ ያስተላለፉት መልዕክት ጥሩ ዜጋ መሆን እንደሚገባቸው፣ ወደ አገልጋይነት እንዲመጡ ሰንበት ት/ቤቶች ማጠናከር እንደሚገባን ፣ከአለባበስ እና ከአነጋገርን ጀምሮ መንጠንቀቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል ። የአንድነቱ መመሥረት ሰንበት ት/ቤትች የልምድ ልውውጥ ማድረግ እንዲችሉ የሰንበት ተማሪዎችን በቃሉ ለማስታጠቅና ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም እንዲሁም የማንበብ ልምዳችንን ማጎልበት የሚቻልበት መንገድ የሚፈጥር በመሆኑ አጽራረ ቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ ለመገዳደር የሚያስችል መሆኑና አያሌ ጥቅሞቹን ዘርዘር አድርገው ገልጸዋል።

የአንድነቱ አባላት አስተያየትና ሃሳብ የሰጡ ሲሆን የእርስ በርስ ትውውቅ መፍጠር ብቁ ዜጋና በሥነ ምግባርና በሃይማኖት ተኮትኩቶ ማድረግ ቢቻል በዕቅድ መመራት ቢቻል ሥርዓተ ትምህርት መማር የሚችሉበት በቀጣይ ለሰንበት ት/ቤት አንድነት ተከታታይ ኮርስ እንዲሰጥ በተመረጡ ርዕሰ ጉዳዮች ትምህርት እንዲሰጥ የጠየቁ ሲሆን የሀገረ ስብከተ ወንጌል ክፍል ተተኪ ሰባኪያን ለማፍራት ሥልጠናውን ከሚመለከተው የሀገረ ስብከቱ ክፍል ጋር ተቀናጅቶ ተግባሩን ለመፈጸም ቃል ተገብቷል።

የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ ሊቀትጉሃን ቀሲስ ሀብታሙ አበበ የሰንበት ት/ቤች አንድነት ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጠው ጥቅም ጥቂቶቹን እንደሚከተለው አቅርበዋል ።

– ዐቅምን ለማስተባበር
በየትም ቦታ ያሉ ሰንበት ት/ቤቶች በተናጠል ለቤተ ክርስቲያን በመስጠት ላይ ያሉት አገልግሎት ከፍተኛ ነው፡፡

– ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ለመጠበቅ
የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ተባብሮ ለመጠበቅ እና ለማስጠበቅ እንደሚረዳ ፡፡

– ልምድ ለመለዋወጥ
የሰንበት ት/ቤቶችን ዕድገት አዝጋሚ ካደረጉት ምክንያቶች ዋነኛው የልምድ አለመለዋወጥ ነው፡፡ አዳዲስ ሰንበት ት/ቤቶች ከቀደምቶቹ ስህተትም ሆነ ጠንካራ ጎን የሚማሩበት አጋጣሚ በጣም አነስተኛ ነው ማለት ይቻላል፡፡

– መንፈሳዊ ጉባኤዎችን በማዘጋጀት፡-
ሰንበት ት/ቤቶች በየሳምንቱ በየደብራቸው ከሚያደርጉት መርሐ ግብር በተጨማሪ እንደ ጊዜው አመቺነት የተወሰነ ወቅት በአንድነት የሚያዘጇቸው ጉባኤያት ቢኖሩ ከፍተኛ ጥቅም ያስገኛሉ፡፡ አያጠያይቅም ፡፡

– የውይይት መድረኮችን በመፍጠር፡-
ከመንፈሳዊ ትምህርት በተጨማሪ ስለ ሰንበት ት/ቤቶች ችግሮችና መፍትሔያቸው፤ ስለ አሠራርና አወቃቀራቸው፤ ስለ ወቅታዊ ሁኔታዎች…ወዘተ የሚነጋገሩበት /የሚወያዩበት/ ጉባኤ ሊዘጋጅ ይገባል፡፡
በውይይትና በጥናታዊ ጉባኤዎቻቸንም ላይ በሚገባ የተጠኑ የመፍትሔ ሐሳብን የሚያመላክቱ ጥናቶች እንዲቀርቡ ሰንበት ት/ቤቶች የዐቅማቸውን መሞከር አለባቸው፡፡

– ትምህርታዊ ጉብኝቶችን በማድረግ፡-
በአሁኑ ወቅት በሰንበት ት/ቤቶቻችን መካከል የአሠራር ልዩነት እንዳለ ይታወቃል፡፡ በርግጥ መሠረታዊ ከሆኑ ጉዳዮች ሌላ የግድ አንድ ዓይነት አሠራር ይኑር ማለት ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም የአሠራር ዘዴው የየሰንበት ት/ቤቶቹን የሰው ኃይል፤ልምድና ዐቅም ይጠይቃልና ነው፡፡

– ዝግጅትን መለዋወጥ
የአንዱ ሰንበት ት/ቤት የተወሰኑ አባላት ወደሌላ ሰንበት ት/ቤት ሄደው ዝግጅቶቻቸውን፤ ትምህርት፤ መዝሙር፤ ሥነ ጽሑፍ፤ድራማ…ቢያቀርቡ መልካም ልምድ የመለዋወጫ አጋጣሚ እንደሚሆን ገልጸዋል።

በመጨረሻም የሰንበት ት/ቤቱን አንድነት የሚመሩ ሥራ አስፈፃሚ የተመረጡ ሲሆን በአባላቱ ፊት ቃለ መሐላ በመፈጸም መርሐ ግብሩ ተጠናቋል።
መረጃው የሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግንኙነት ነው።