ጥር ፯ ቀን ፳፻፲ወ፮ ዓ.ም
“””””””””””””””””””””””
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ
******
በዓለ ጥምቀትን አስመልክቶ የሚተላለፉ መልእክቶች የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ ላይ ብቻ ያተኮሩ እንዲሆኑ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የባህር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መመሪያ አስተላልፈዋል።
ብፁዕነታቸው በተለያዩ ቋንቋዎች ለተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቃለ መጠይቅና ምላሽ እንዲሰጡ ለተመረጡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በሰጡት አባታዊ መመሪያ የቅድስት ቤተክርስቲያን መልእክት የሚተላለፈው በማእከል በመሆኑ የማእከሉን መልእክት ብቻ እንዲያስተላልፉ መመሪያ የሰጡት ብፁዕነታቸው ከግል አስተያየት መቆጠብ እንደሚገባም አበክረው ገልጸዋል።
ቤተክርስቲያናችን የሰላም ሰባኪ እንደመሆኗ መጠን የቤተክርስቲያን መልእክት ሲተላለፍ ሰላም ላይ ማተኮርና በዓል ለማክበር የሚወጡ ምእመናን በዓሉ በሰላም አክብረው እንዲመለሱ መልእክት ማስተላለፍ እንደሚገባ ግልጽ መመሪያ ሰጥተዋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያዊ ሁሉም ሃይማኖቶች ተከባብረው የሚኖሩባት ሀገር መሆኗ ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱ ይህ በዓል የሚከበርባቸውን ቦታዎች ለማጽዳትና ሥርዓት ለማስከበር ጥረት እያደረጉ ያሉ የሌሎች ሃይማኖት አባላትን በአባትነት ያመሰገኑት ብፁዕነታቸው ታቦታቱ በሚያልፉባቸው መንገዶች የሚገኙ የሌሎች ቤተ እምነቶችን ማክበር እንደሚገባ ለሁሉም ካህናትና ምእመናን አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እየተላለፈ ያለውን የበዓል አከባበር ክልከላን የሚገልጹ የሐሰት ዜናዎች ቤተክርስቲያንን የማይወክሉና ቤተክርስቲያናችን በዓሉን በሰላም ለማክበር ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር እያደረገች ያለውን ጥረት ከግንዛቤ ያላስገባ መሆኑን ብፁዕነታቸው አሳውቀዋል።