ሐምሌ 23/2016 ዓ.ም (ዲላ)
በዲላ ማረሚያ ተቋም ውስጥ በሚገኘው በቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ቤተክርስቲያን በመምህር ኤልያስ ተምረው ለጥምቀት የተዘጋጁ 47 የሚሆኑ በብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬ ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ተጠምቀው የእግዚአብሔር ልጅነትን አገኙ።
በዕለቱም የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራአስኪያጅ መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ የሀገረ ስብከቱ ስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ ሊቀትጉሃን ቀሲስ ሀብታሙ አበበ የመንበረ ጵጵስና ወናጎ ወረዳ ቤተክህነት ዋና ሥራአስኪያጅ ሊቀጠበብት መሪጌታ መሠረት ዋና ፀሐፋ ሊቀ ህሩያን ቀሲስ እሸቱ ዋለ ተገኝተዋል ።
#ሐምሌ 23/2016 ዓ.ም በተደረገው ሥርዓት በመምህር ኤልያስ አረጋ ትምህርተ ሃይማኖት ለ6ት ተከታታይ ወራት የተማሩ 67 ክርስቲያኖች የምረቃ መርሐ ግብር ተደርጓል። ትምህርታቸውን በአግባቡ ይከታተሉ ለነበሩ ክርስቲያኖች የምስክር ወረቀት ተዘጋጅቶ የተሰጠ ሲሆን ከ1-3 ለወጡ ሽልማትም ተበርክቶላቸዋል ።
በብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬ ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የመጽናኛ ትምህርተ ወንጌል የሰጡ ሲሆን የእግዚአብሔር ልጅነት ስላገኙ ደስ ሊላቸው እንደሚገባ ገልጸዋል። እንዲሁም በቀጣይ በሃይማኖታቸው እንዲጠነክሩ ከኃጢአት እንዲርቁ መልካም ሥራ እንዲሰሩ አባታዊ ምክር ሰጥተዋል።
በዲላ ማረሚያ ተቋም በቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ቤተክርስቲያን ቅዳሜና እሁድ በመመላለስ ያለመሰልቸት ሐዋርያዊ ተግባሩን የተወጣው መምህር ኤልያስ አረጋ ያለምንም ምንዳ ይኸን በጎ ተግባር ስለተወጡ ልዩ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል ምስጋናው ይገባቸዋል።
በዲላ ማረሚያ ተቋም በሚገኘው በቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ቤተክርስቲያን ብዙ ኦርቶዶክሳውያን ታራሚዎች ሲገኙ ተከታታይ የሆነ ትምህርተ ወንጌልና ወር በገባ 4 እና በየሳምንቱ እሁድ የቅዳሴ አገልግሎት ያገኛሉ።
ሁላችንም የወንጌል አገልግሎቱ በተጠናከረ መልኩ እንዲከናወን የሚቻለንን ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅብን ተመላክቷል።