ጥር ፮ ቀን ፳፻ ፲ወ፰ ዓ.ም
=================
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
“”””””””””””””””””””””””””

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በፒያሳና በአራት ኪሎ የሚገነቡትን የቤተክርስቲያናችን ሕንጻዎች በጨረታ ላሸነፉ ኮንትራክተሮች ሳይተቶቹን አስረክዋል።

በዛሬው ዕለት የሳይት ርክክብ የተደረገላቸው ሳይቶች ፒያሳ አካባቢ የሚገነባው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዝክረ ቅዱሳን ህንጻ G+7አንዱ ሲሆን የግንባታ ሥራውን ለማከናወን ምንሀር ኮንስትራክሽን የተባለው ሕንጻ ተቋራጭ አሸንፎ ሳይቱን የተረከበ ሲሆን አራት ኪሎ አካባቢ ከጠቅላይ ቤተክህነት ጀርባ ባለው ስድስት ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ሕንጻ አበው በሚል ስያሜ ለሚገነባው B3+G+12 ሁለገብ ሕንጻ ደግሞ አተም ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ የተባለው ኮንትራክተር አሸናፊ በመሆን ሳይቱን ተረክቧል።

በሁለቱ ቦታዎች የሚገነቡት ሕንጻዎች ማለትም በአራት ኪሎ አካባቢ የሚገነባው ሕንጻ በሰላሳ ወራት፣ ፒያሳ አካባቢ የሚገነባው ሕንጻ ደግሞ በሃያ ወራት ውውጥ ተገንብተው የሚጠናቀቁና አገልግሎት ላይ የሚውሉ መሆናቸው ታውቋል።

በሳይት ርክክቡ ወቅት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት ቤተክርስቲያን የምታስገነባቸውን ሕንጻዎች ለመሥራት አሸናፊ በመሆናችሁ እድለኞች ናችሁ ካሉ በኋላ የግንባታ ሥራውን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ በጥራትና በፍጥነት በመሥራት እንድታስረክቡ አደራ እንላለን ብለዋል።

በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የጠቅላይ ቤተክህነት መምሪያ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።