“ቤተክርስቲያን የተፈተነችበት ሥርዓቷን እና ልጆችዋን ያጣችበት ጊዜ ስለሆነ ለሀገራችን እና ለቤተ ክርስቲያናችን ሰላም እንዲመጣ የጷጉሜን ፮ቀናት ወደ እግዚአብሔር እንጸልይ።” ብፁዕ አቡነ አብርሃም

ነሐሴ ፳፱ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም
******
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
“””””””””””””””””””””

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የጷጉሜን ፮ ቀናት ጸሎተ ምህላ እንዲኖር አወጀ።

ዛሬ ነሐሴ ፳፱ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም በብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና በአቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባህርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በተሰጠው መግለጫ መሰረት የጷጉሜን ወር ፮ ቀናት መላው ኦርቶዶክሳዊ በጸሎት እና በምህላ እንዲያሳልፍ መታወጁን ነው የገለጹት።

በመግለጫውም ዘመኑ ከደስታ እና የምስራች ይልቅ ሀዘንን የምንሰማበት ዘመን ስለሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን የተቸገሩትን የተራቡትን ፣ የተፈናቀሉትን እና የተጎዱትን እያሰቡ በጾም እና በጸሎት እንዲያሳልፉ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ 13ተኛ ወር በሆነችው ወርሐ ጷጉሜ እለተ ምጽዓትን የምናስብበት ፤ ሠማይ የሚከፈትበት ፤ ጸሎት የሚሰማበት ሚስጥራዊ የሆነች ወር ነችና የበደሉንን ይቅር ብለን በንጹሕ ልቦና የቻልን ጾመን ያልቻልን በጸሎት እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት እና የምንለምንበት ወር ሊሆን ይገባል ሲሉ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ገልጸዋል።

ብፁዕነታቸው የቤተ ክርስቲያን በዓላት ሲደርሱ ከሥርዓቷ እና ከአስተምሮዋ ውጪ በ ሆነ መልኩ የተለያዩ አካላት የዳንኪራ ጥሪ በማዘጋጀት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አግባብነት የሌለው መሆኑን እና ምዕመናንም ከዚህ እንቅስቃሴ እራሳቸውን ሊያርቁ ይገባል ነው ያሉት።

የማትደፈረዋን እና የማትነካዋን ቤተክርስቲያን የሚነኩ ሰዎች በዝተዋል ፤ ቀጣዩ ዓመትም ኢትዮጵያውያን በሰላም በፍቅር የምንኖርበት የሚራቡ የሚፈናቀሉ የሚያዝኑ ሰዎች እንዳይኖሩ ሁሉም ምዕመን ጠዋት ኪዳን ከሰዓት በሠርክ ጸሎት በየአብያተ ክርስቲያን በመሄድ ያልቻለም በየቤቱ ሊጸልይ ይገባል ብለዋል።