በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ወቅታዊ ችግር ምክንያት አዋሽ ሰባት በእስር ላይ የሚገኙ ወጣቶችን ሁኔታ ለመመልከት ብፁአን አባቶች የሚመሩት ልዑክ በማረሚያ ቤቱ ጉብኝት እንደሚያደርግ ቤተክርስትያኗ ያቋቋመችው ጊዜያዊ የሕግ ኮሚቴ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
በማረሚያ ቤቱ የታሰሩ ወጣቶች ያሉበትን ሁኔታ ለመከታተል አስቸጋሪ እንደሆነ የተናገሩት የኮሚቴው አባል የሕግ ባለሙያና ጠበቃ አያሌው ቢታኒ፣ ወጣቶች ያሉበትን ሁኔታ ለማየትና ተከታይ የሕግ ሂደቶችን ለማስጀመር ቦታው ድረስ መሄድ አስፈላጊ ሆኖ እንደተገኘ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በቦታውም ከበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች በተለይም ከአዲስ አበባና በዙሪያዋ ካሉ አካባቢዎች ታፍነው የተወሰዱ በርካታ ወጣቶች እንደሚገኙ ተግሯል፡፡
የሕግ ኮሚቴው እስካሁን ድረስ በአዋሽ ሰባት የታሰሩ 268 ወጣቶች እንዳሉ ሪፖርት የደረሰው ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ የአቃቂ ቃሊቲ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ሕብረት ሰብሳቢ የሆነው ዳዊት ጉታ ብቻ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እንደታየለት ጠበቃው ተናግረዋል። ወጣቱም በፍርድ ቤት የዋስ መብቱ ተከብሮለት እደተፈታ የተናገሩት ጠበቃው፤ ከእሱ ውጭ ጉዳያቸው በፍርድቤት የታየላቸው ወጣቶች እንደሌሉ ተናግረዋል፡፡