ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በወቅታዊ ጉዳይ በጄኔቭ፣ ስዊትዘርላንድ ከዓለም አብያተክርስቲያናት ምክር ቤት ጸሐፊ ቄስ ፕሮፌሰር ዶ/ር ጄሪ ፒሌ ጋር በወቅታዊ የቤተክርስቲያናችን ጉደይ ውይይት አደረጉ።

ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በወቅታዊ ጉዳይ በጄኔቭ፣ ስዊትዘርላንድ ከዓለም አብያተክርስቲያናት ምክር ቤት ጸሐፊ ቄስ ፕሮፌሰር ዶ/ር ጄሪ ፒሌ ጋር በወቅታዊ የቤተክርስቲያናችን ጉደይ ውይይት አደረጉ።
++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና የመገናኛ ብዙኀን ሥርጭት አገልግሎት ድርጅት የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ጥር ፳፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም ጄኔቭ፣ ስዊትዘርላንድ በሚገኘው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት በመገኘት ከዋና ጸሐፊው ቄስ ፕሮፌሰር ዶ/ር ጄሪ ፒሌ ጋር ውይይት አደረጉ። ብፁዕነታቸው ዋና ጸሐፊው በቅርቡ ለዚህ ከፍተኛ ሃላፊነት በመመረጣችው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ስም የደስታ መልእክት አስተላልፈዋል። ቤተ ክርስቲያናችን የምክር ቤቱ መስራችና ንቁ አባል በመሆን የበኩልዋን ሚና እየተወጣች መሆኑን አስታውሰው ይህ ግንኙነት ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ብፁዕነታቸው ቤተ ክርስቲያናችን የገጠማትን ወቅታዊ ሁኔታ ያብራሩላቸው ሲሆን የችግሩ ዋነኛ ምንጭ የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀኖና እና ሕግጋት የጣሱ ጥቂት አፈንጋጭ አካላት ድርጊታቸው በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕልውና ላይ የሚያስከትለውን ታላቅ አደጋ በመገንዘብ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተወገዙና የተለዩ ቢሆንም መንግስት የሕግ የበላይነትንና የሕዝብን ሰላም የመጠበቅ ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ ከፍተኛ ሃዘንና ጭንቀት ፈጥሯል። በዚህም ጳጳሳት እየተሳደዱ፣ ካህናተ እየታሰሩ፣ ምዕመናን እየተደበደቡ ይገኛሉ። እንዲህም ሆኖ ሕግ የጣሱት አካላት በንስሐና በይቅርታ ቢመለሱ ቤተ ክርስቲያን በሯን ክፍት አድርጋ እየጠበቀች ትገኛለች። ምክር ቤቱ ለቤተ ክርስቲያናችን ተቋማዊ ልዕልና፣ ለሕግ የበላይነት፣ ለሰላምና ለፍትሕ አጋርነቱን እንዲገልጽ ብፁዕነታቸው ጠይቀዋል።

ዋና ጸሐፊው ለተደረገላችው ዝርዝር ማብራሪያ አመስግነው ይህች ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን በወቅቱ የገጠማት ፈተና በእጅጉ አንደሚያሳስባቸውና ጉዳዩን በቅርበት መከታተላቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። በመጨረሻም በብጹዕነታቸው በኩል ለቅዱስ ፓትርያርካችን ሰላምታና መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል። ከብፁዕ አባታችን ጋር መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ሃይለ ጊዮርጊስ በስዊትዘርላንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያን አስተዳዳሪና የጄኔቫ አጥቢያ ሰበካ ጉባኤ አመራር ተወካዮች በውይይቱ ተሳትፈዋል።

ውይይቱን ተከትሎ ዋና ጸሀፊው በማግስቱ አጋርነታቸውን የሚያሳይ መግለጫ አውጥተዋል። በመግለጫቸው ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዘመነ ሐዋርያት የተመሰረተች፣ ሁልጊዜም ለአንድነትና ለሰላም የደም መስዋዕትነትም ጭምር ስትከፍል የኖረች ናት ብለዋል። አዲስ ሲኖዶስ ለመመስረት በሚደረገው ሙከራ ማዘናቸውን አክለው የቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት እንዲጠበቅ በጸሎት እግዚአብሔርን ጠይቀዋል። የሚመለከታቸው የፖለቲካ ሃይላት ሁሉ ሕጋዊ ሰውነት ያላት ቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጉዳይዋን ባላት መንፈሳዊ ቀኖና እና ህግ ለመፍታት ብሎም የምዕመናኗን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ የምታደርገውን ጥረት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ዝርዝር መግለጫውን በዚህ ማስፈንጠሪያ ያንብቡ። https://www.oikoumene.org/news/wcc-expresses-solidarity-with-ethiopian-orthodox-tewahedo-church