ብፁዕ አቡነ አብርሃም ወቅታዊ የቤተክርስቲያንን ሁኔታ አስመልክቶ የሰላም ጥሪ አተስላለፉ።
ሐምሌ ፲፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም አዲስ አበባ
ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ወቅታዊ የቤተክርስቲያናችንን ሁኔታ አስመልክቶ ዛሬ ሐምሌ ፲፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም ከቀትር በኋላ በጽ/ቤታቸው ልዩ መግለጫ ተሰጥተዋል።
ብፁዕነታቸው ባስተላሐፉት የሰላም ጥሪ በክልል ትግራይ አህጉረ ስብከት ለሚገኙ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት አንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያንን በጽናት ለማገልገል በጋራ የገቡትን ቃልኪዳን በማስታወስ በተደጋጋሚ የተደረገላቸውን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉ ደግመው አሳስበዋል።
ብፁዕነታቸው እንደገለጹት ከሆነ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል፣ በትግራይ ክልልና በአማራ ክልል ያለውን ውጥረት ለማርገብ ጥረት እናድርግ የሚል የሰላም መልዕክት ባስተላለፍንበት ወቅት በክልል ትግራይ አህጉረ ስብከት የተመደቡ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ትግራይ ሰላም መሆኗንና ደም ወደሚፈስባቸው ሌሎች አካባቢዎች እንድናተኩር ሲያሳስቡን ቆይተዋል ብለዋል።
ይሁን እንጂ በትግራይ ክልል የደረሰው ጉዳት ቤተክርስቲያንን እጅግ ያሳዘነ በመሆኑ የመልሶ ማቋቋም ሥራውን በጋራ መሥራት ይቻል ዘንድ መፍትሔው ተቀራርቦ በአባትነት መንፈስ መመካከር እንጂ በሕገ ቤተክርስቲያን ከተደነገገው ውጪ ኤጲስ ቆጶሳትን መሾም ባለመሆኑ ለውይይት በራቸውን እንዲከፍቱ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በትግራይ ክልል የሚገኙ ሊቃውንት የቤተክርስቲያናችንን ቀኖናና ሥርዓት መሠረት በማድረግ ከቤተክርስቲያን ጎን እንዲቆሙ ጥሪአችንን እናስተላልፋለን ያሉት ብፁዕነታቸው በትግራይ አህጉረ ስብከት የተጀመረውንም ቤተክርስቲያንን የመክፈል አዝማሚያ በመጽሐፍ መሠረትነት እንዲሞግቱና በክልሉ የሚገኙ አባቶች እያካሔዱት ካለው ጠቃሚነት የሌለው ተግባር እንዲቆጠቡ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል።
የፌደራል መንግሥትም ሆነ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አሰተዳደር መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አንገባም በሚል አመክንዮ በክልል ትግራይ አህጉረ ስብከት የተመደቡ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን በተመለከተ ዝምታን ቢመርጡ በቤተክርስቲያናችን ላይ በሚደርሰው መከፈል ከታሪክ ተጠያቂነት እንደማይድኑ በመግለጽ የማሸማገል ተግባራቸውን እንዲወጡ አባታዊ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም ምእመናን በዚህ አስጨናቂ ወቅት ያላቸውን ቅሬታ ሁሉ ትተው ከቤተክርስቲያን ጎን እንዲቆሙ የቤተክርስቲያናችን ወዳጆችም እንደ እስከአሁንኑ ሁሉ ቤተክርስቲያንን እንዲያግዙ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።