ታኅሣሥ ፩ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
++++++++++++++

ብፁዕ  አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፥ የባህር ዳርና ሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ዻዻስ በእስራኤል ቴልአቪቭ ቤንጎርዮን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ ብፁዕ  አቡነ ዕንባቆም በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ገዳማት ሊቀ ጳጳስና የገዳማቱ  አበው መነኮሳት ደማቅ አቀባባል አድርገውላቸዋል።

ብፁዕነታቸው በዚህ ሐዋርያዊ ጉዟቸው በቅድስት ሀገር  ኢየሩሳሌም ገዳማት በመገኘት የገዳማቱን የሥራ እንቅስቃሴ የሚጎበኙ ሲሆን ገዳማቱ አንድነታቸው ተጠብቆ  የሚያካሒዱት አገልግሎት ሁሉ ሰላምና ፍቅር የነገሠበት ሆኖ የበለጠ ተጠናክሮ መበጠል የሚችልበትን መንገድ መሰረት ያደረገ ምክክር  እንደሚያደርጉ ታወቋል።

የገዳሙን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የበለጠ ለማስፋፋትና ለማጠናከርም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ዻዻስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በሚሰጡት አባታዊ መመሪያ እና ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ጋር በሚኖሩ የጋራ ሥራዎች ዙሪያም ጥልቅ ውይይት በማድረግ የገዳሙ ሰላምና አንድነት፣ የማኅበረ መነኮሳቱ ኅብረት ተጠብቆ አገልግሎቱ እንዲቀጥል ማድረግ የሚያስችል አስተዳደራዊ መመሪያ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ብፁዕ አቡነ አብርሃም ለአምስት ቀናት  በእስራኤል በሚኖራቸው  የአምስት ቀናት ሐዋርያዊ አገልግሎት ቆይታ  ከእስራኤል የሃይማኖትና የቱሪዝም ሚኒስትሮችና በእስራኤል ከሚገኙ የአይሁድ እምነት መሪዎች ( ራብአዮች) ጋር  በመገናኘት በልዩ ልዩ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚመክሩ ታውቋል።

ፎቶ EOTC TV