ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በሀገረ ስብከታቸው የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉዞ አጠናክረው ቀጥለዋል።

ጥር 6 ቀን 2016 ዓ.ም
***
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
“””””””””””””””””””””

ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የሀገረ ስብከቱና ፣የቤተመጻሕፍት ወመዘክር፣የማኅበራት ማደራጃ  መምሪያ ሊቀ ጳጳስ በአላማጣና አካባቢው የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ አገልግሎት አጠናክረው በመቀጠል ቅዳሜ ጥር 4 ቀን 2016 ዓ.ም  በዋጃ አካባቢ በሚገኘው ደብረ ሣሌም ቦታ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ሲደርስሱ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

በዚሁ ጊዜም በአካባቢው በነበረው በጦርነት ምክንያት በሞተ ሥጋ  ለተለዩ አሥራ አምስት ሰዎት ጸሎት አድርሰዋል።በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በሕዝበ ክርስቲያኑ አማካኝነት እየተሰራ የሚገኘውን ሕንጻ ቤተክርስቲያን ተዛውረው የተመለከቱት ብፁዕነታቸው ሕዝበ ክርስቲያኑ  በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ  ችግቹን ችሎና ታግሶ ይህን የመሰለ ሕንጻ ቤተክርስቲያን መስራቱ ከሰማዕትነት የሚያስቆጥረው መሆኑን ገልጸው ለሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ማሰሪያ አንድ መቶ ሺህ ብር በመለገስ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተዋል።በዚሁ ጊዜም ሕዝበ ክርስቲያኑ አንድነቱን አጽንቶ የቅዱስ ሲኖዶስን መመሪያ ጠብቆና አክብሮ በመገኘቱ አመስግነዋል።

በመቀጠልም አዲስ ወደ ተሰራው አየር ማረፊያ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የተጓዙት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የዋዜማ ሥርዓተ ቡራኬ በማድረግ የማጽናኛ ትምህርት የሰጡ ሲሆን በማግስቱ ጥር 5 ቀን 2016 ዓ.ም ቅዳሴ ቤቱን በማክበር ትምህርተ ወንጌልና ቃለ ቡራኬ ሰጥተዋል።በዚሁ ጊዜ ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክትም ሕዝበ ክርስቲያኑ በጦርነት ውስጥ ሆኖ ይህንን የመሰለ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ሰርቶ ማስመረቁ ከሰማዕትነት በላይ መሆኑን አይተናል አድንቀናልም ብለዋል።

በዚሁ ጊዜም የሕንጻ አሰሪ ኮሚቴውና ምዕመናኑ የብር መስቀል ለብፁዕነታቸው አበርክተውላቸዋል።
ብፁዕነታቸውም የሃያ ሺህ ብር የበረከት ስጦታ አበርክተዋል።በመጨረሻም በብፁዕነታቸው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።

ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በዚህ መልኩ የቀጠሉት ብፁዕነታቸው ዛሬ ጥር 6 ቀን 2016 ዓ.ም ወደ ኮረም ከተማ የተጓዙ ሲሆን ግራት ካህሱን አለፍ እንዳሉ ከአምስት መቶ በላይ በሚሆኑ መኪናዎችና ባጃጆች እንዲሁም በእግር ጭምር በመሆን ሕዝበ ክርስቲያኑ በተለይም ደግሞ ወጣቶች በነቂስ ወጥተው ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ብፁዕነታቸውም የኮረም ከተማን ተዛውረው ከባረኩ በኋላ በኮረም  ቅድስት ማርያም  ቤተክርስቲያን ኪዳን አድርሰዋል።በአውደ ምህረቱም ሦስት ሊቃውንት ቅኔ አበርክተውላቸዋል፤ካህናቱና ምዕመናንም በወረብ፣ በዝማሬና በእልልታ በአክብሮት ተቀብለዋቸዋል።
ብፁዕነታቸውም ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋናቸውን በማቅረብ ችግሮቹ ተወግደው ተወልደው ባደጉበት አገር ከሚወዳቸውና ከሚያከብራቸው ሕዝባቸው ጋር ለመገናኘት በመብቃታቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ እግዚአብሔርን አመስግነዋል ።

በዚሁ ጊዜም ብፁዕነታቸው “ምንም እንኳን በሞት ጥላ ብሆንም አንተ ከእኔ ጋር ነህና አልፈራም”በሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል መነሻነት ሰፊ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል።በጦርነቱ ለሞቱ ወገኖችም ጸሎት ያደረጉት ብፁዕነታቸው  አዲስ ለሚታነጸው የመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያንም የመሰረት ድንጋይ አኑረዋል።ለሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ግንባታ የሚውል የአንድ መቶ ሺህ ብር ስጦታ ያበረከቱት በብፁዕነታቸው ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት ቤተክርስቲያን አንዲት ስለሆነች የቤተክርስቲያናሁን አንድነት እንደጠበቃችሁና የቅዱስ ሲኖዶስን ድምጽ በአንድነት እንደቆማችሁ ሁሉ አሁንም ይህንኑ ተግባራችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ አደራ እላለሁ ብለዋል።

በመጨረሻም ሁተሰበሰበው ሕዝበ ክርስቲያን ቃለ በረከትና ቃለ ምዕዳን በመስጠት የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ህኖ ብፁዕነታቸው ወደ መንበረ ጵጵስናቸው አቅንተዋል።