ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጀርመንና አካባቢው እና የምሥራቅ ጎጃም አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መጋቢት ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ ም በጀርመን ሙንስትር ከተማ በመገኘት ከካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሙንስተርና አካባቢ ጳጳስ ከኾኑት ዶክተር ፊልክስ ጌን ጋር ውይይት ውይይት ማድረጋቸውን የሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል በላከልን ዘገባ ገልጿል።

በውይይታቸውም ብፁዕነታቸው የቤተ ክርስቲያናችንን ወቅታዊ ሁኔታ ለሊቀ ጳጳሱ በሰፊው አብራርተውላቸዋል። በተጨማሪም ሀገረ ስብከቱ በጀርመን ለመመሥረት በአስበው ገዳም ዙሪያና ይህንኑ አስመልክቶ ቤተ ክርስቲያን በምትፈልገው እርዳታ ዙሪያ ገለጻ አድርገውላቸዋል። በሙንስተር ከተማ ስላለው የመንበረ ንግሥት በዓታ ለማርያም አጥቢያ ጉዳይም ውጤታማ ውይይት አድርገዋል።

በኹሉም ጉዳዮች የብፁዕነታቸውን ማብራሪያ የሰሙት ሊቀ ጳጳስ ዶ/ር ጌንም ጽ/ቤታቸው በሁሉም ጉዳዮች ላይ በተቻለው ዐቅም አብሮ እንደሚሠራ፣ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግም ቃል ገብተውላቸዋል።

የሙንስተር ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሀገረ ስብከት በጀርመን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ከሚገኙት አኅጉረ ስብከት የኮለንን ሀገረ ስብከት ተከትሎ በሁለተኛ ደረጃ ብዙ ካቶሊካውያን የሚገኙበት ሀገረ ስብከት ነው።ዘገባው የጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ነው።