መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም
+ + +
ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስ በሀገረ ስብከቱ እየተከናወኑና ወደፊት ሊተገበሩ በታቀዱ ዕቅዶች ዙሪያ በአዲስአበባ ከተማ ከሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ጋር በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ የነገረ መለኮት መማሪያ ክፍል የጋራ ውይይትና ምክክር አደረጉ።
ለምክክሩ መነሻ የሚሆን ሰነድ የቀረበ ሲሆን በሰነዱ በሀገረ ስብከቱ ታሪካዊ ጉዞ፣ አሁናዊ ሀገረ ስብከቱ ያለበት ነባራዊ እውነታና ተግዳሮት፣ ወደፊት በሀገረ ስብከቱና በምእመናን መሥራት ያለበትን ተግባራት፣ የተሳታፊዎች ድርሻና አስተዋጽኦ ዙሪያ ሰፋ ያለ ሰነድ በፓወር ፖይንት ቀርቧል። ብፁዕነታቸው እስካሁን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ማዕከል ከተማ ተኮር በመሆኑ የተነሳ በገጠር ያለው ብዙ ቁጥር ያለው ምእመናን ካህን፣ መምህርና ሰባኬ ወንጌል ባለመኖሩ በትምህርት እና ጠባቂ በማጣት ወደ ተለያዩ ቤተ እምነት እንዲሄዱ ምክንያት የሆነና ሂደቱም እየቀጠለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ከተመሠረተ ጥቂት ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን በተለይ በሀገረ ስብከት ደረጃ የ10 ዓመት ስልታዊ ዕቅድ ታቅዶ ወደ ተግባራዊ ሂደት መግባቱ አንዱ ማሳያ በመሆኑ ይህን ሀሳብ ለመላው ማህበረሰብ መድረስ እንዳለበት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል። እንደ ሀገረ ስብከት የቀረበው ጥናቱ ችግሮቹን በሙሉ የለየ ከመሆኑ በተጨማሪ የመፍትሔ ሃሳብ የተቀመጠ በመሆኑ ወደ ሥራ መግባት ያስፈልጋል ብለዋል ።
በአዲስአበባ የሚኖሩ የቅድስት ቤተክርስቲያን ልጆችም በቀረበው የውይይት ሰነድ መነሻነት ሃሳብ የሰጡ ሲሆን በቀጣይ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት በሃሳብ ፣በገንዘብ ፣በእውቀት እንዲሁም ሌሎችንም በማስተባበር ጭምር እገዛ ለማድረግ ቃል ገብተዋል። ይህ መድረክ ቀጣይነት ያለው ሲሆን ሁሉም ኦርቶዶክሳውያን በገንዘባቸው በእውቀታቸው በሙያቸው ሀገረ ስብከቱን እንዲደግፉ ጥሪ የቀረበ ሲሆን በመጨረሻም በጉባኤው ማጠቃለያ ሶስት አባላት ያሉት አስተባባሪ ኮሚቴ በማቋቋም በብፁዕነታቸው ጸሎትና ቡራኬ ተጠናቋል።
መረጃው የሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ነው