ሰኔ 09 ቀን 2016 ዓ.ም
አዳማ /ናዝሬት/ኢትዮጵያ

በመጋቢ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ “ርጢን” እና በዲያቆን ያረጋል አበጋዝ “የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወቱና ትምህርቱ በሚል ርዕስ የታተሙትን ሁለት መጽሐፍ ወደ አፋን ኦሮሞ በመ/ር ደሳለኝ ብርሃኑ ተተርጉመው ባዛሬው ዕለት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ ቋሚ አባል የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምና የሥራ አመራር መንፈሳዊ ኮለጅ የበላይ ኃላፊ በኢትዮጵያ የሁሉም ሃይማኖቶች ተቋማት የቦርድ ሰብሳቢ በተገኙበት በልዩ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ተመርቋል።

በዕለቱ የሀገረ ስብከቱ የየመምሪያ ክፍል ኃላፊዎች፣ የወረዳ ቤተክህነት ሊቃነ ካህናት ፣ የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች ሊቃውንተ ቤተክርቲያን ፣የፍሬ ሃይማኖት ሰንበት ት/ቤት፣ የማኀበረ ቅዱሳን አዳማ ማዕከል አባላትና ዘማርያን እንዲሁም በርካታ እንግዶች ተገኝተዋል።

በተተረጎሙት መጽሐፍት ዙሪያ በዲያቆን ሀብታሙ እና በቀሲስ ገ/ሥላሴ የደሰሳ ጽሑፍ ቀርቧል። ተርጓሚው ሌሎች መጽሐፍትን ተርጉመው ያዘጋጁ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን እነኝህን የትርጉም መጽሐፍት ለህትመት እንዲበቁ በብፁዕነታቸው ብር 50, 000 ሺህ ብር ድጋፍ ተደርጓል። በማያያዝ የወረዳ ቤተክህነት ሊቃነ ካህናት በገዳማትና በአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የሰበካ ጉባኤ አባላትና የክብር እንግዶች የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል።

ብፁዕነታቸው ይህን የትርጉም ሥራ ተጠናክረው እንዲቀጥል አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈው  ለእነዚህ የትርጉም ሥራ መሳካት የበኩላቸው ለተወጡ ላገዙና ተርጓሚው መምህር ደሳለኝ ብርሃኑን ጨምሮ ምሥጋና አቅርበው በብፁዕ አባታችን አቡነ ጎርጎርዮስ የምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቃለ ምዕዳን እና ቡራኬ የመርሐግብሩ ፍፃሜ ሆኗል