መጋቢት ፲፩ ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም

መጋቢት ፲፩ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር የሆኑት ዶክተር ፈርድናንድ ቮን ዌይሂ በኢትዮጵያ በአዲስ አበባ የተመደቡበትን የሥራ ኃላፊነት ለመጀመር ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሲሆን፤ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ጋር ትውውቅ አድርገዋል፡፡

አምባሳደሩ እንደተናገሩት “ለእኔ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የበለጠ መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም በዚህች ሀገር ውስጥ ስለ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ማወቅ ለብዙ ሰዎች በጣም ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለዚህ እኔም በተያዘልኝ ቀጠሮ መሠረት ከጀርመን ኤምባሲ በመምጣት ከቅዱስ ፓትርያርኩም ቡራኬ ተቀብዬ ስለ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለማወቅ ችያለሁ” ብለዋል፡፡

አምባሳደሩ አያይዘውም “በአሁኑ ወቅት የዐቢይ ጾም ወቅት በመሆኑ፤ ኦርቶዶክሳውያን በጾም፣ በጸሎት በየአብያተ ክርስቲያንቱ ነው ያሉት፡፡ ይህ ሥነ ሥርዐት በጀርመን ሀገር ከምናየው የተለየና አስደናቂ ነው፡፡ በተዘዋወርኩባቸው ቦታዎች ሁሉ በተለይም አብያተ ክርስቲያናት በሚገኙባቸው ቦታዎች በየዕለቱ ሰው በቤተክርስቲያን ይገኛል፣ የሚሰማው የቅዳሴ ድምፅ የተለየ ነው፡፡ይህ በጣም አስደናቂ ተሞክሮ ነው።” ብለዋል፡፡

አምባሳደሩ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጋር በትብብር ስለሚሠሩት ሥራም አብራርተዋል “የልምድ ልውውጥ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ አንድ መጥቀስ የምፈልገው ነገር ቢኖር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ልማት ኮሚሽን ጋር ስለ ደን ጥበቃ በትብብር የምንሠራው ሥራ አለ፡፡ በኢትዮጵያ ክልል በአየር ስትበሩ አንዳንድ አረንጓዴ ጥቅጥቅ ያሉ የደን ደሴቶችን ታያለህ። በዚህ ደሴት መካከል ቤተክርስቲያን አለች፡፡ ቤተክርስቲያን ደኖችን ጠብቃ ያቆየቻቸው ናቸው፡፡ ሰዎችም ቤተክርስቲያኗ የምታስተምረውንም ስለሚሰሙ ዛፎችን አይቆርጡም፡፡ ስለዚህ ስለ ደን ጥበቃ የቤተክርስቲያኗ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡እኔ እንደማስበው እነዚህን አረንጓዴ ደሴቶች በመሬት ገጽታ ላይ ማስቀመጥ እና የበለጠ ማማስፋት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ እናም ይህንን አረንጓዴነት በመደገፍ አብረን እንሠራለን” ብለዋል፡፡

በመጨረሻም አምባሳደር ዶክተር ፈርድናድ ቅዱስነታቸው በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ስላነጋገሯቸው፣ በተደረገላቸው አቀባበልና ቅዱስነታቸው ስለሰጧቸው ቡራኬ አመሰግነዋል።

©EOTC T.V.