መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
•ብፁዕ አቡነ አብርሃም
የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
•ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና በሰሜን አሜሪካ የኒዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
•ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳስት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤
•የየመምሪያውና የየድርጅቱ ኃላፊዎች፣
•የየሀገረ ስብከቱ ተወካዮች፣
•የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣
•ከልዩ ልዩ ክፍለ ዓለማት የመጣችሁ እንግዶች፣
•በአጠቃላይ በዚህ ዓቢይ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ የተገኛችሁ በሙሉ
እግዚአብሔር አምላካችን ከዓመት ዓመት አድርሶ ይህን የተቀደሰ ቀኖናዊ ጉባኤ ለማካሄድ ስለሰበሰበን ክብርና ምስጋና ለሱ እናቀርባለን እናንተንም እንኳን ደኅና መጣችሁ እንላለን፡
“በብዙኅ ሕማም ሀለወነ ንባኣ ለመንግሥተ እግዚአብሔር” ወደ እግዚብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ይገባል (የሐ.ሥራ 14፥22)
ይህ የቅዱስ መጽሐፍ አስተምህሮ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት ጠንካራ ጥረትና ጽናት የሚያስፈልግ መሆኑን የሚያስገነዝብ ገዢ አስተምህሮ ነው ከቅዱስ መጽሐፍም ከታሪክም በትክክል ተመዝግቦ እንደሚገኘው የቤተክርስቲያን ጉዞ ገና ከጅምሩ አንሥቶ በጸዊረ መስቀል የታጀበ ነው
ጸዊረ መስቀል ምንም የመረረ ቢሆንም ተሸንፎ ግን አያውቅም ነገረ መስቀል በአሸናፊነት እንጂ በተሸናፊነት አይታወቅምና ነው ቅዱሳን ሐዋርያት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ መግባት አለብን ሲሉ የመከራ መስቀል ዓጸፋ አሸናፊነትና መዳን መሆኑን ስለሚያውቁ ነው በሀገራችንም ሆነ በመላው ዓለም ዙሪያ ያሉ ክርስቲያኖች የተለያዩ ጸዋትወ መከራዎችን በመቀበል የሚገኙት ከመንፈስ ቅዱስ ኃይልና ከሐዋርያት ተጋድሎ ባገኙት ውርስ ነው፡፡
•ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣
•ክቡራን የጉባኤው ተሳታፊዎች!!
እንደ ዕድል ሆኖ ዘመናችን በመከራ መስቀል የታጀበ ሆኖ ይታያል ብዙ ክርስቲያኖች በአሁኑ ጊዜ በዚህ ፍኖተ መስቀል እያለፉ ነው አብያተ ክርስቲያናት እየተቃጠሉ፣ ካህናትና ምእመናን እየተፈናቀሉ፣ እየተሰደዱና እየተገደሉ ነው ሌላም ጫና ሁሉ እያንገላታቸው ነው ይህ ሁኔታ ሄዶ ሄዶ ሃይማኖቱን የሚያዳክም ነው ሃይማኖቱ ሲደክም ደግሞ ኢትዮጵያዊ ማንነትና ባህል አብሮ ይደበዝዝና አለን ብለን የምንመካበት ዕሤት በሙሉ ነበረ ወደ ማለት ይቀየራል ታሪኩን ሃይማኖቱንና ባህሉን ሥነ ምግባሩንና ትውፊቱን ያጣ ወይም የማያውቅ ትውልድም ይተካና ሁሉም በጨለማና በድንግርግር ይዋጣል
ይህ ዓይነቱ የሃይማኖት የታሪክ የማንነትና ባህል ውድቀት እንዳያጥለቀልቀን ጠንክሮ መስራት ዛሬ ከምንም ጊዜ በላይ ይጠበቅብናል የኛ ዐቅም ከመንፈስ ቅዱስ መንጭቶ በምእመናን ልቡና የሚመላለስ ኃይል ስለሆነ ይህንን ዐቅም ለመጠቀም ከሁሉ በላይ ምእመናንን በእንክብካቤ መያዝ ያስፈልገናል በዘመነ ሰማዕታት ቤተክርስቲያንን በፀዊረ መስቀል ያሻገሯት ካህናትና ምእመናን እንደፈትልና ሰም ተዋሕደው ነው ለምእመናን የምናቀርበው አገልግሎት ሁሉ የምእመኑን ልብ የሚረታና ለሃይማኖቱ በፍጹም ልቡ ታማኝ ሆኖ እንዲቆም የሚያስችል ሊሆን ይገባል፡፡
•ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣
•ክቡራን የጉባኤው ተሳታፊዎች!!
ሁላችንም እንደምንገነዘበው አጠቃላይ የሰበካ ጉባኤ ዓላማ በተወሰነ የንዋይ አሰባሰብ ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን በቤተክርስቲያኒቱ ዙሪያ መለስ ተልእኮ ላይ የሚሠማራ ዓቢይ ተልእኮ ነው በተለይም በምእመናን ህልውናና ደኅንነት ላይ አብዝቶ መስራት ያስፈልጋል ምእመናን ካሉ ሁሉም አለ ምእመናን ከሌሉ ግን ሁሉም የለም ይህንን ሁላችንም በትኲረት ልንገነዘብ ይገባል፡፡
ሌላው ልናልፈው የማንችል ታላቅ ነገር የቤተክርስቲያናችንን አንድነት ነው በቤተክርስቲያን አንድነት እንደዚሁም በሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ይዘቱ ላይ ጥያቄ ያለው ሰው ይኖራል ብለን አንገምትም በዚህም ብዙ ልዩነት አናይም ነገር ግን በአንዳንድ አስተዳደራዊና ዘመን ወለድ ቅሬታዎች አንድነታችን እየተፈተነ ነው ይህ የማንም ስሕተት ሳይሆን በውስጣችን የተፈጠረ ዕንቅፋት ነው
በመሆኑም ይህ እየተፈታተነን የሚገኘው የአንድነት ፈተና በተለመደው የቅዱስ መጽሐፍ አስተምህሮ በጥበብና በብልሐት ማረም ግድ ይለናል ቅሬታ ብቻ ሳይሆን የቅሬታ መፍቻም አለና እሱን ተጠቅመን አንድነቱን ማምጣት አለብን ተለያይቶ መኖር ያሳፍራል ያዳክማልም እንጂ በየትኛውም መመዘኛ ብርታት ይሰጣል ተብሎ አይገመትም ስለሆነም ቅሬታን በድርድርና በውይይት በይቅርታና በመተማመን ዘግተን አንድነታችንን ማጽናት አለብን፡፡
•ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣
•ክቡራን የጉባኤው ተሳታፊዎች!!
ቤተክርስቲያናችን ወደ ፊት ተራምዳ ታላቁ ተልእኮዋን በአግባቡ እንዳትወጣ ካደረጋት አንዱ የአሰራር ስልታችን እንደሆነ ማንም አይስተው በመሆኑም ይህንን ዘመኑን የማይዋጅ የአሰራር ስልታችን ለማሻሻል የሚያስችል፣ ሊመራና አቅጣጫ ሊያመላክት የሚችል መሪ ዕቅድ እንዲዘጋጅ በቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑ ይታወቃል በውሳኔው መሠረት የመሪ ዕቅድ ሰነድ ተዘጋጅቶና ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ ይሁንታ አግኝቶ በአሁኑ ጊዜ የሥርጸትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ
በመሆኑም መሪ ዕቅዱ፣ አሰራራችንን መልክ በማስያዝ፣ ለውጤት በሚያበቃ አተገባበርና አፈጻጸም በመከተል በመናበብና በመግባባት ልንጠቀምበት ይገባል ሃይማኖትን ከመንካት በቀር ሃይማኖታችንን ለማስጠበቅ የሚያስችለንን የዘመኑ ቴክኖሎጂ (የአሰራር ጥበብና ዘዴ) በሙሉ ተጠቅመን መምራት ጊዜው የሚጠይቀው ቊልፍ ተግባር ነው
ከዚህ ሌላ ትንሽም ሆነ ትልቅ ስራ መስራትና ውጤት ማስመዝገብ የሚቻለው ሰላም ሲኖር ነው ሀገራችንን ጨምሮ በአካባቢያችን የሚገኙ ጎረቤቶች በሰላም እጦት እየተንገላቱ ነው ስለሆነም አሁንም አብዝተን ወደ አምላካችን በመጸለይ፣ ስለ ሰላም ስለ አንድነትና ስለ ወንድማማችነት ፍቅር ደጋግመን ልናስተምርና ልንጮህ ይገባል መንግሥታችንም የአብያተ ሃይማኖት ደኅንነት የካህናትና የምእመናን የመኖር ዋስትና የሁሉም ዜጎች ሰላማዊ ኑሮ በማስፈን ለአካባቢው ሰላም የበኩሉን እንዲወጣ፣ ሕዝቡም ለዚሀ አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጥ በዚህ አጋጣሚ በቤተ ክርስቲያናችን ስም ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
በመጨረሻም
በዚህ ዓለም ዐቀፋዊና ዓመታዊ የቤተክርስቲያናችን አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ለመገኘት ከሀገር ውስጥና ከተለያዩ ክፍለ ዓለማት የመጣችሁ ሁላችሁም በድጋሚ እንኳን ደኅና መጣችሁ እያልን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን 32ኛውን አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በጸሎት የተከፈተ መሆኑን እናበስራለን፡፡
እግዚአብሔር የተባረከና የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን፤
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓመተ ምሕረት
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ