ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ጾመ ፍልሰታን በማስመልከት ያስተላለፉት መልእክት፣ ቃለ በረከትና ቡራኬ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይነበባል። መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
በሀገር ውስጥና በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ!

በማሕፀነ ማርያም በፈጸመው እውነተኛ ተዋሕዶ የሰው ልጅን ከኃሣር ወደ ክብር የመለሰ እግዚአብሔር አምላካችን፣ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ስድስት ዓመተ ምሕረት ጾመ ቅድስት ማርያም በደኅና አደረሰን አደረሳችሁ!፤

‹‹ተፈሥሒ ኦ ምልእተ ጸጋ፣ ተፈሥሒ እስመ ረከብኪ ሞገሰ በኀበ እግዚአብሔር፡- ምልእተ ጸጋ ሆይ ደስ ይበልሽ፤ በእግዚአብሔ ዘንድ ሞገስን አግኝተሻልና ደስ ይበልሽ›› (ሉቃ. 1÷28-30″)
የክብር አምላክ እግዚአብሔር የሰው ልጅን ከወደቀበት ዐዘቅተ ኵነኔ የሚያድንበት ዕድል እንዳዘጋጀ በብሉይ ኪዳን በስፋት ገልፆል፤ የማዳን ስራውም ከሰው ወገን ከሆነች ቅድስት ድንግል በሚወለደው መሲሕ እንደሚፈጸም አስረድቶአል፤ የማዳን ቀኑ በደረሰ ጊዜም መልእክቱን በፊቱ በሚቆመው በቅዱስ ገብርኤል በኩል ልኮአል፤ ቅዱስ ገብርኤልም የተነገረውን መልእክት ለድንግል ማርያም አድርሶአል፡፡

ቅዱስ ገብርኤል ለድንግል ማርያም እንዲነግር ከታዘዘባቸው መካከል ‹‹ጸጋን የተመላሽ ደስተኛይቱ ሆይ÷በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን አግኝተሻልና ደስ ይበልሽ›› የሚል አስደናቂ መልእክት ይገኝበታል፡፡

የተወደዳችሁ ሕዝበ ክርስቲያን!

ከእግዚአብሔር መንጭቶ በቅዱስ ገብርኤል በኩል ለድንግል ማርያም የተነገረ ይህ መልእክት፣ የቅድስት ድንግል ማርያምን ክብር ከመግለጽ ባሻገር ለሰው ልጆች ሁሉ ያለው ፋይዳ በእጅጉ የላቀ ነው፤

‹‹ጸጋ›› የሚለው ቃል እንደ ቅዱስ መጽሐፍ አስተምህሮ ያልተወሰነ፣ ገደብና ቅድመ ሁኔታ የሌለው ስጦታን ሲያመለክት ‹‹ሞገስ›› የሚለው ቃል ደግሞ ተወዳጅነትን ተደማጭነትን ተሰሚነትን የሚያመለክት የክብርና የባለሟልነት መግለጫ ቃል ነው፡፡

እነዚህ ቃላት ከእግዚአብሔር ዘንድ በቅዱስ ገብርኤል በኩል ለቅድስት ድንግል ማርያም ተነግረዋል፤ የእግዚአብሔር ቃል የማይለወጥ ነውና ቃላቶቹ ለድንግል ማርያም ቃል ኪዳን ሆነው የተሰጡ ናቸው፤ የተሰጡበትም ምክንያት ሰውን ለማዳን ስራ እንዲውሉ እንጂ ለሌላ አይደለም፡፡

ምክንያቱም የእግዚአብሔር የማይናወጥ ፈቃድ ሰውን ማዳን ነውና፤ በመሆኑም ቅድስት ድንግል ማርያም ከእግዚአብሔር በተሰጣት በዚህ ገደብ የሌለው ቃል ኪዳኗ ሰውን ልትታደግ በቅታለች፤ይህም በቃና ዘገሊላ ባደረገችው ምልጃ በጭንቀት የተዋጡትን ሠርገኞች እንዴት እንደታደገች በቅዱስ ወንጌል ተጽፎ እናገኘዋለን፤ቅድስት ድንግል ማርያም ቀድሞውኑም ከፍ ያለ ሞገስ ተሰጥቶአታልና የሠርጉ አሳላፊዎችን ‹‹የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ›› በማለት ስታዝዝ እናያለን፤ ይህ ለሰው ልጆች ሁሉ የተሰጠ አስደናቂ የትድግና ስጦታ ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን!

የድንግል ማርያም የጸጋ ስጦታ በብሥራተ ገብርኤል ተገልጾ፣ በቃና ዘገሊላ ተተግብሮ በዕለተ ስቅለት ‹‹እነሆ ልጅሽ፣ እነኋት እናትህ›› በሚል መለኮታዊ ማኅተም የታተመ ነው፤ ይህ ቃል እሷ እናታችን መሆኗን፤ እኛም ልጆችዋ መሆናችንን ያረጋገጠ ማኅተመ ቃል ኪዳን ነው፤ የቃል ኪዳኑ ይዘት እሷ በአማላጅነቷ እንደ ልጅ ልትንከባከበን እኛም እንደ እናት ልናከብራትና ልንማፀናት የሚገባን መሆኑን ያሳያል፤ የእናትነትና የልጅነት ማረጋገጫ የሆነ ይህንን የቃል ኪዳን ማኅተም ሊሰርዝም ሆነ ሊፍቅ ሊደመስስም የሚችል ኃይል የለም፡፡

ይህ ጸጋና ሞገስ በምድር ብቻ ሳይሆን በሰማይም የሚቀጥል እንጂ የሚገደብ አይደለም፤ ሞት፣ ቦታና ዘመንም አይወስኑትም፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን በሞት በቦታና በዘመን አይገደብምና ነው፤ ‹‹ኪዳኑንም ለዘለዓለም ያስባል›› ተብሎ የተገለጸውም ለዚህ ነው፤ (መዝ. )111÷5)
መንፈስ ቅዱስም በእሷ አንደበት ‹‹እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ነሽ ይሉኛል›› በማለት የተናገረው ይህንን ለማስረዳት እንደሆነ ማስተዋል ያሻል፡፡

በእግዚአብሔር ተሰጥቶ፣ በቃል ኪዳን ታትሞ፣ በቅዱስ ገብርኤል ተብራርቶ፣ በጌታችን ተረጋግጦና በሐዋርያት በኩል የተላለፈልን፣ ሰውን ማዳን ግቡ የሆነ የድንግል ማርያም ምልጃ ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊት፣ በሁሉ ያለች፣ አንዲትና ቅድስት ኦርቶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ሺሕ ዓመታት ያህል አምና እና ተቀብላ ስትጠቀምበት ኖራለች፤ አሁንም በዚሁ ትቀጥላለች፡፡

በኦርቶዶክሱ ዓለም ዛሬ የሚጀመረው የጾመ ማርያም ሱባዔም የዚሁ ጭብጥ ማሳያ ነው፤ ዋናው መልእክቱም ድንግል ማርያም በተሰጣት ጸጋና ሞገስ በጸሎቷ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትንና ይቅርታን የምታሰጠን ስለሆነች እሷን በመማፀን ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ የሚል ሆኖ ይመሰጠራል፡፡

የተወደዳችሁ ሕዝበ ክርስቲያን ልጆቻችን!

ጾም ፈቃደ ሥጋን በማድከምና ፈቃደ ነፍስን በማጎልበት ምሕረተ እግዚአብሔር መሻታችንን የምናሳይበት መንፈሳዊ ማመልከቻ ነው፤ ጾም ከጥንት ጀምሮ የነበረ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኝ ድልድይ ነው፤ ቀደምት አበው በጾም ምክንያት ከጥፋት ድነዋል፤ የለመኑትንም አግኝተዋል፤ ምስጢርም ተገልጾላቸዋል፤ ዲያብሎስም ድል አድርገውበታል፡፡

እኛም ዛሬ ጾምን ስንጾም በሀገራችንም ሆነ በአካባቢያችን ብሎም በዓለም ዙሪያ ሁሉ ስጋትን እየጫረ ያለው የጥፋት እንቅስቃሴ እግዚአብሔር እንዲያስቆምልን ከልብ በመጸለይ ሊሆን ይገባል፤ ይህንንም ስናደርግ በጸሎት ብቻ ሳይሆን ንስሐ በመግባትና ቅዱስ ቁርባንን በመቀበል እንደዚሁም የሰላም የፍቅርና የዕርቅ ሰው ሆኖ በእግዚአብሔር ፊት በመቆም ሊሆን ይገባል፡፡

ችግሮችንና አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ በውይይትና በምክክር ለመፍታት የሚደረገው ጥረትም በእጅጉ ሊደገፍ ይገባል፤ ግጭትና ጦርነት ከሚያጠፋን በቀር ሊያተርፍልን የሚችል አንዳች ጥቅም የለም፡፡

በመሆኑም በየትኛውም የሀገራችን አካባቢ ያላችሁ ልጆቻችን እባካችሁ ለሰላም ለውይይትና ለሰው ልጆች መብት መከበር ቅድሚያ ስጡ፤ ግድያ፣ ዕገታ፣ አብያተ ሃይማኖትን መዳፈር፣ ዘረፋና ቅሚያ፣ የሴት ልጅን መድፈርና ሰውን ማንገላታት አቁሙ፤
እነዚህ ድርጊቶች ሰብአዊነትን ዝቅ የሚያደርጉ፣ እግዚብሔርን የሚያስቆጡ፣ በታሪክም የሚያሳፍሩ ናቸው፤ እነዚህን ሳናርም የምንጾመው ጾም ትርጉም ስለሌለው ንስሐ ገብተን ከእንደዚህ ያለው ድርጊ ርቀን ጾሙን መጾም ይገባል፤ ይህን ስናደርግ ጾማችን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋ ይኖረዋል፡፡

በመጨረሻም
የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ በተለይም በጾመ ማርያም ሱባዔ በንስሐና በጸሎት የሚያሳልፉ ሕዝበ ክርስቲያን ስለ ሃይማኖት መጠበቅ፣ ስለሀገር ሰላምና አንድነት፣ እንደዚሁም ስለሕዝቦች ደኅንነትና ጤንነት አጥብቀው እንዲጸልዩ በእግዚአብሔር ስም መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡
መልካም የሱባዔ ወቅት ያድርግልን
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ነሐሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም.
ዋሽንግተን ዲሲ – ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ