ጷጉሜን ፪ቀን፳፻ ፲ወ፮ዓ.ም
=================
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
“””””””””””””””””””””””

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሰሜን አሜሪካ ሲያካሒዱት የቆዩትን ሐዋርያዊ አገልግሎት አጠናቀው ዛሬ ማለዳ ወደ አገራቸውና ወደ መንበረ ክብራቸው ተመልሰዋል።

ቅዱስነታቸው ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራአስኪያጅ የባህርዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ፣ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣፣መልአከ ሕይወት አባ ኃይለገብርኤል ነጋሽ፣የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጸሐፊ፣የጠቅላይ ቤተክህነት መምሪያ ኃላፊዎች ደማቅ አቀባበል ድርገውላቸዋል።

በመቀጠልም ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቀጥታ ወደ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ጉዞ የተደረገ ሲሆን በገዳሙ የቅዱስነታቸውን መምጣት ሲጠባበቁ በነበሩ የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣በካህናት፣በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና በምዕመናን ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።በዚሁ ጊዜ በሊቃውንትና በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችም ያሬዳዊ ዝማሬዎች ቀርበዋል።

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የባህርዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የእንኳን ደህና መጡ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በመልዕክታቸውም ቤተክርስቲያን ከሙስና፣ ከአድሎ አሰራር እንድትርቅና የቀደመ ክብሯ ተጠብቆ እንዲቆይ ተደጋጋሚ መመሪያ በመስጠት ክብሯ እንዲጠበቅ ሲያደርጉ መቆየትዎ ይታወቃል። ስለሆነም የቤተክርስቲያንን ክብር የሚነኩ ብልሹ አሰራሮች ሁሉ ተወግደው የቤተክርስቲያን ክብሯና ስሟን ለማስጠበቅ መስራት ይኖርብናል፤ ያሉት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ለዚህም የቤተክርስቲያን ክብር ለማስጠበቅ ሲባል መክፈል ያለብንን መስዋዕትነት ሁሉ ከፍለን የቤተክርስቲያናችንን ክብርና ልዕልና በማስጠበቅ ቤተክርስቲያናችንን ጤናማ ተቋም አድርገን ማስቀጠል እንችል ዘንድ ገለልተኛ ከሆኑና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ሰርተን ክብሯን እናስጠብቃለን ብለዋል።

ከኮሪደር ልማት ጋር በማያያዝም ከከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ክብርት አዳነች አቤቤ ጋር በመነጋገርና በመመካከር ፍጹም መግባባትን መሰረት ባደረገ አግባብ የቤተክርስቲያንን ክብርና መብት በሚያስጠብቅ መልኩ አስፈላጊውን የልማት ሥራ ሁሉ በማከናወን ላይ እንገኛለን በማለት መልዕክታቸውን አጠቃለዊል።

በመጠረሻም ቅዱስነታቸው ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል በማመስገን በክረምቱ ጊዜ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የተፈጠረውን የመሬት መንሸራተትን ተከትሎ በወገኖቻችን ላይ በደረሰው አደጋ ፍጹም ማዘናቸውን ገልጸው ከሰላም ማጣቱና ከችግሩ ጋር ተዳምሮ የደረሰው አደጋ እጅግ አሳዛኝ መሆኑን ጠቁመው ልዑል እግዚአብሔር ሰላሙን፣ፍቅሩን አንድነቱንና ስምምነቱን እንዲሰጠም እንጸልያለን ካሉ በኋላ በብፁዕ አቡነ አብርሃም በምሬት የተገለጸውን ጉዳይ በተመለከተ በጥናት ላይ በተመሰረተ መልኩ ችግሩን ለመፍታት ቅዱስ ሲኖዶስ ይመክርበታል በለዋል።

በማያያዝም ብፁዐ አቡነ አብርሃም አጠገባቸው ያሉ የሚረዷቸው ሰዎች በሌሉበት እኛም ባልነበርንበት ጊዜ በትዕግስትና በጥበብ ሥራቸውን በማከናወንና ቤተክርስቲያንን በመምራት ላሳዩት ትጋት ምስጋና ይገባቸዋል በማለት ምስጋና ካቀረቡ በኋላ አባታዊ ቃለ ምዕዳንና ቃለ ቡራኬ ሰጥተው የአቀባበል መርሐ ግብሩ ተጠናቋል።