በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ብፁዕ አቡነ አብርሃም
የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የባሕር ዳርና
የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤
የተከበራችሁየመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያውና የየድርጅቱ ኃላፊዎች፤
የአዲስ አበበ ሀገረ ስብከት ኃላፊዎች፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ተወካዮች፤
ከሀገር ውስጥና ከውጭ የመጣችሁ የየሀገረ ስብከቱ ኃላፊዎችና ተሳታፊዎች፤
በአጠቃላይ በ43ኛው ዓመታዊ ዓለም ዐቀፍ የጠቅላላ መንፈሳዊ ጉባኤ ለመሳተፍ በዚህ የተገኛችሁ በሙሉ፤
“አሠንዩ ፍኖተ ዘተሰመይክሙ ኖሎተ ከመ ትርዓዩ መርዔተ ከመ ዐሠርቱ ወክልኤቱ ሐዋርያቲሁ እለ መሀሩ በስሙ፡- ኖሎት የተባላችሁ ሆይ በስሙ እንዳስተማሩ እንደ ዐሥራ ሁለት ሐዋርያት መንጋውን ትጠብቁ ዘንድ መንገድን አሳምሩ” (ቅዱስ ያሬድ)
በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው ሹመት ወይም ኃላፊነት ካለ ተጠያቂነት የማይቀር ጉዳይ ነው፤ ምክንያቱም ሹመት የሚሰጠው ስራ እንዲሰራበት እንጂ እንዲሁ ለከንቱ ስላልሆነ ማለት ነው፡፡

ሹመት የመፈጸምና የማስፈጸም ሕጋዊ መሳሪያ ነው፤ መሳሪያውን በአግባቡ ከተጠቀምንበት የምንመሰገንበት፣ ያ ካልሆነ ግን የምንወቀስበት፣ ምናልባትም የምንቀጣበት አጋጣሚ ሊያስከትል ይችላል፤ ይህም በየጊዜው በሥዩማን ላይ ሲደርስና ሲፈጸም የምናየው እውነታ ነው፡፡ እኛ ካህናትና ምእመናን የእግዚአብሔርን መንግሥት ተልእኮ ልናስፈጽም በሕዝበ እግዚአብሔር ላይ የተሾምን ሥዩማን ነን፤ የመንግሥተ እግዚአብሔር ተልእኮ ከሰው ወገን አንድ ስንኳ እንዳይጠፋ መጠበቅ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የልጅነት ሥልጣን የተሰጠን እኛ ወደ መንግሥቱ በረት ያልገቡትን የማስገባት፣ ገብተው የወጡትን መልሶ የማስገባት፣ በበረቱ ያሉትን በጥሩ ውሀና በለመለመ መስክ በማሰማራት የመጠበቅ ኃላፊነት አለብን፡፡

ይህንን ኃላፊነታችን በትክክል ለመወጣት ከሁሉ በፊት እኛ ሥዩማን ተልእኮአችንን በውል መገንዘብ አለብን፤ ለተመደብንበት ተልእኮም በጽናት መቆም አለብን፣ በትጋትም መስራት ይጠበቅብናል፤ ከዚህም ጋር በእምነት በሥነ ምግባር በሥራ አፈጻጸም ከምንጠብቃቸው መንጋዎች በእጅጉ የላቅን ሆነን መገኘት በጣም አስፈላጊያችን ነው፡፡ በመንግሥተ እግዚአብሔር ተሹሞ ወደሥራ የተሠማራ ሰው ሥራው ፍጹም የተቃና ይሆንለት ዘንድ “ራሱን ክዶ” መስቀሉን መሸከም ግድ ይለዋል፤ ያለዚያ ውጤታማ መሆን አይቻልም፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት!
የተከበራችሁ እንግዶች!
አሁን ያለነው ሥዩማን በዚህ ዘመን ላለችው ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያት ሆነን የተሾምን ነን፤ ወደ በረቱ ያልገባ፣ ገብቶም የወጣ ካለ ማስገባትና መመለስ ያለውም በተመቻቸ መልካም አስተዳደር፣ በለመለመ ትምህርተ ወንጌል፣ በጥሩ ሥነ ምግባር አርአያ ሆኖ መጠበቅ ከኛ ይጠበቃል፡፡ ታድያ ይህንን በተግባር መተርጐም ችለናል ወይ? በጎቻችን አልቦዘኑም ወይ? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ከሁላችን ይጠበቃል፡፡
ይህ ዓቢይ ጉባኤ የተሰበሰበበት ምክንያትም ይህንን ተልእኮ ለማስፈጸም በሚደረገው ጥረት ያጋጠሙ ነገሮች ካሉ ለመስማትና ለመገምገም እንደዚሁም የመፍትሔ አቅጣጫ በማስቀመጥ በተቀመጠው መሪ ዕቅድ አማካኝነት ተልእኮውን ለመወጣት ነው፤ ‹‹የሚደርስበትን የማያውቅ የሚሄድበትን አያውቅም›› የሚለው ብሂል በአሠራራችን ቦታ እንዳይኖረው መጠንቀቅ አለብን፡፡

በአሁኑ ጊዜ የቤተ ክርስቲያናችን መዳረሻ የማይታወቅ አይደለም፤ ቤተ ክርስቲያናችን በቀጣዮቹ ዐሥር ዓመታት የት ልትደርስ እንደምትችል ቅዱስ ሲኖዶስ ባጸደቀው መሪ ዕቅድ በግልጽ ተቀምጦአል፤ ይህ መሪ ዕቅድ ሁላችንም ትኵረት ሰጥተን ለተግባራዊነቱ መረባረብ ይኖርብናል፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት!
የተከበራችሁ እንግዶች!
እንደ እውነቱ ከሆነ አሁን ባለን ክህነታዊ አገልግሎትና አስተደደር ክፍተቶች እንዳሉን የማይካድ ነው፤ ዘመኑ የፈጠረብን ጫና ሳያንስ በውስጣችን ያሉ ግልጽነት የጐደላቸው አሰራሮችም ለተልእኮአችን ከባድ ዕንቅፋት እየሆኑብን ነው፡፡ ሰበካ ጉበኤ የተቋቋመው በተዘረጋው መዋቅር አማካኝነት ቤተ ክርስቲያንን በማኅበረ ካህናት ወምእመናን የጋራ ጥበቃ ለአዲሱ ትውልድ ለማሸጋገር እንደሆነ ሁላችን አንስተውም፡፡ ይሁን እንጂ በቤተ ክርስቲያናችን ይህን ያህል የመልካም አስተዳደር ክፍተት እየታየ የሰበካ ጉባኤ ዓላማ ግቡን መትቶአል ለማለት ስለማያስደፍር በዚህ ዙሪያ ያሉትን ችግሮች በሙሉ ሊቀርፍ የሚችል አሰራር ቀይሶ ችግሩን ለመቀልበስ በጥናት ላይ የተመሠረተ ዘላቂና ፈጣን መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት!
የተከበራችሁ እንግዶች!
ያለፈው ዓመት በዝቋላ ገዳምና በሌሎች አካባቢዎች አበው መነኮሳት፣ ቀሳውስት እንደዚሁም በርከት ያሉ ምእመናን በግፍ የተገደሉበት ሆኖ አልፎአል፤ አሁንም ችግሩ እየቀጠለ ነው፤ በቅርቡም በምሥራቅ ሸዋ ከነቤተሰባቸው የተገደሉ አዛውንት ካህን ሁናቴ የችግሩን ቀጣይነት ይጠቁማል፡፡
በመጨረሻም፤
በሀገር ውስጥና በውጭ የምትገኙ ካህናትና ምእመናን ልጆቻችን፣ የቤተ ክርስቲያናችን አንድነትና ሃይማኖት፣ ቀኖና እና ሥርዓት ተጠብቆ እንዲቀጥል ለማስቻል በሚደረገው ጥረት ሁላችንም ተባባሪ እንድንሆን፣ በሀገራችን ያለው አለመግባባት በሰላምና በውይይት ተፈትቶ ፍጹም ሰላም ይሰፍን ዘንድ በጸሎትና በአንድነት እንድትተጉ አባታዊ መልእክታችንን እያስተላለፍን 43ኛው ዓመታዊ ዓለም ዓቀፍ ጠቅላላ መንፈሳዊ ሰበካ ጉባኤ በዛሬው ዕለት የተከፈተ መሆኑን እናበስራለን፡፡
መልካም ጉባኤ ያድርግልን፤

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ጥቅምት ፬ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ