ሚያዝያ ፳፩ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””””””
አዲስ አበባ- ኢትዮጵያ
***
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት “አሜን ኢትዮጵያ” የተሰኘው ሀገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅት የሰው ልጆች ወንድማማችነት /እኅትማማችነት / ለዓለም ሰላም እና አብሮ መኖር “በሚል መሪ ቃል በBest Western Plus Hotel ባሰናዳው የውይይት መርሐ ግብር ላይ ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን ጋር ተገኝተው ሰላም ለሰው ልጆች ሕይወት ያለውን ጥልቅ ትርጉም በማብራራት ካለፈው ጊዜ በመማር በምድራችን ላይ ሰላም ሰፍኖ የሰው ልጆች በነፃነት መኖር እንዲችሉ ሁሉም ጥረት ማድረግ እንደሚኖርበት በማሳሰብ አባታዊ ቃለ በረከት አስተላልፈዋል ።
መርሐ ግብሩ በየዓመቱ ሲዘጋጅ የዚህኛው ዓመት ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን የዘንድሮውን ልዩ የሚያደርገው በታላቅ ድምቀት በቅርቡ የተከበረውን የብፁዕ ወቅዱስነታቸውን 10ኛ ዓመት በዓለ ሢመት ምክንያት በማድረግ ቅዱስነታቸው በዘመነ ክህነታቸው ስለ ሰላም ላደረጉት አባታዊ ጥረት እውቅና በመስጠት በምስጋና ለማክበር ጭምር መሆኑ በመድረኩ አስተባባሪዎች ተገልጿል።
በዝግጅቱ ላይ ከቅዱስነታቸው በተጨማሪ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ እና ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተገኝተው መልእክት አስተላልፈዋል።ሲል የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽሕፈት ቤት በላከልን ዘገባ ገልጿል።