መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም
*****
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የኢኮኖሚ አቅሟን በተለያዩ የልማት ሥራዎች በማጎልበት ተቀዳሚ ተልዕኮዋ የሆነውን ስብከተወንጌልን ማስፋፋት፣የገጠር አብያተክርስቲያናትን የማጠናከር፣የአብነት ትምህርት ቤቶችን የማስፋፋትና የማጠናከር ሥራዋን ለማቀላጠፍ ያስችላት ዘንድ በተለምዶ ባሻ ወልዴ ችሎት በመባል በሚታወቀው ቦታ ላይ በአንድ ዓመት ውስጥ ያስገነባችው ዘመናዊ አፓርታማ ተጠናቆ በዛሬው ዕለት የቁልፍ ርክክብ ተደርጓል።

በርክክብ ሥነሥርዓቱ ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቤተክርስቲያን ከመንፈሳዊ አገልግሎቷ በተጓዳኝ በተለያዩ የልማት ዘርፎች በመሰማራትና ኢኮኖሚያዊ አቅሟን በማሳደግ በመንፈሳዊው ዘርፍ ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነች መሆኗን ገልጸዋል።

ቤተክርስቲያን በሕንጻ ግንባታዎች ላይ በመሰሚራቷም ለበርካታ ወገኖች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር በርካታ ወገኖችን መጥቀሟን የገለጹት ብፁዕነታቸው በቤት ችግር ምክንያት የሚንገላቱ ወገኖችም የመኖሪያ ቤት የሚያገኙበትን ዕድል ከመፍጠር አልፋ ለከተማችን አዲስአበባ ገጽታ ግንባታም ዓይነተኛ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች ብለዋል።

ዛሬ የቁልፍ ርክክብ የሚደረግለት ይህ ሕንጻ በብፁዕ አቡነ ያሬድ የጠቅላይ ሥራ አስኪያጅነት ጊዜ ተጀምሮ በአንድ ዓመት ውስጥ በመጠናቀቁ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ቀደም ተብለው የተጀመሩና የግንባታ ሥራቸው በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተጓተቱት ሁለት ሕንጻዎችን በተቻለ ፍጥነት ለማጠናቀቅ የሚያስችል ሥራ የተሰራ በመሆኑ በቅርብ ጊዜ የግንባታ ሥራቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቁ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው አሁን የተጠናቀቀው ሕንጻም በህጋዊ የጨረታ ሥርዓት ለተጠቃሚዎች ይተላለፋል ብለዋል።

በአንድ ዓመት ውስጥ የግንባታ ሥራው ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ የሆነው ይኸው ህንጻ 21ክፍሎች ያሉት እያንዳንዱ ክፍልም 3 መኝታ ቤቶች፣ ሊፍትና ጄኔሬተር ያለው ሲሆን ቴራሱ በሕንጻው ላይ ለሚኖሩ ነዋሪዎች ልዩልዩ ዝግጅቶች የሚያገለግል ይሆናል፤ከዚህ በተጨማሪም ሕንጻው የእሳት ማጥፊያ እና የውሀ ፓንፕ የተገጠመለትና ከወዳጅነት ፓርክ ፊለፊት ለመኖሪያ ምቹ በሆነ ሥፍራ ላይ የሚገኝ ሕንጻ ነው።

የሕንጻ ግንባታ ሥራውም በአተም ኮንስትራክሽንና በዘዶር አማካሪ ድርጅት የተገነባ ሲሆን ለዚህ ሕንጻ ግንባታ በታቀደለት ጊዜ መጠናቀቅም የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅና የሥራ ኃላፊዎች ሚና የጎላ ነው።

ብፁዕ አቡነ ያሬድ በዘመነ ሢመታቸው ይህን ሕንጻ ግንባታን ጨምሮ በድሬዳዋ ከተማ ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃውን ባለ አራት ወለል የገበያ ማዕከልና በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በመገንባት ላይ የሚገኘውን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ግንባታዎችን በማስጀመር ለብፁዕ አቡነ አብርሃም ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ማስረከባቸው ይታወሳል።

በርክክብ ሥነሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁን ጨምሮ ፣ም/ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ፣የጠቅላይ ቤተክህነት መምሪያ ኃላፊዎች የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የሕንጻ ሥራ ተቋራጩና የአማካሪ ድርጅቱ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በድሬደዋ ከተማ የተገነባው ሁለገብ የገበያ ማዕከል እና በዛሬው ዕለት የቁልፍ ርክክብ የተደረገለት ህንጻ የምርቃት መርሀ ግብር ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በበዐለ ሀምሳ ውስጥ እንደሚከናወን ከቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።