መጋቢት ፲፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
+++++++++++++++++++
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
==============

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የባህር ዳርና የሰሜን ጎጃመረ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በአሮጌው ቄራና በጠቅላይ ቤተክህነት በመገንባት ላይ ያሉትን ሕንጻዎች የሥራ አፈጻጸም  ተዛውረው ከተመለከቱ በኋላ በቀጣይ ሥራዎች ዙሪያ መመሪያ ሰጥተዋል።

ብፁዕነታቸው በአሮጌው ቄራ በመገንባት ላይ የሚገኙትን  ሁለት ሕንጻዎች ተዘዋውረው ከተመለከቱ በኋላ የግንባታ ሥራዎቹ  በፍጥነት ተጠናቀው አገልግሎት ላይ መዋል ይችሉ ዘንድ የሕንጻ ሥራ ተቋቋራጮቹ ፣ተቆጣጣሪዎቹና የግንባታ ሥራውን በቅርበት የሚከታተለው የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የሥራ አመራሮች የግንባታ ሥራው ጥራትና ፍጥነትን መሰረት በማድረግ የሚከናወንበትና  ሥራው በፍጥነት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የሚችልበትን ስልት ተከትለው እንዲሰሩ አደራ ብለዋል።
በግንባታ ሥራዎቹ የሚስተዋሉ ችግሮች ሁሉ መወገድ እንዲችሉም ተናቦና ተግባብቶ መስራት እንደሚገባ የገለጹት ብፁዕነታቸው በግንባታ ሥራው ሂደት የሚስተዋሉ ችግሮችን በመንቀስ እንዲታረሙና  ለግንባታ ሥራ ተቋራው ፍጥነትና ጥራትን መሰረት በማዶረግ እንዲሰራ አመራር ሰጥተዋል።

በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በመገንባት ላይ የሚገኘው ዘመናዊ፣ግዙፍና ሁለገብ አዳራሽ የሥራ ሂደትን የተመለከቱት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የግንባታ ሥራው በመልካም አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።ብፁዕነታቸው ሠላሳ አራት ፐርስንት ላይ ደርሶ የተረከቡት ይኸው የግንባታ ሥራ የፕላን ማሻሻያ የተደረገበት ሲሆን ይኸንኑ ተከትሎ በተገኘው  ከሦስት መቶ ካሬ ሜትር  በላይ በሆነው ትርፍ ቦታ ላይ ዘመናዊና ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ያሟላ የቅዱስ ሲኖዶስ መሰብሰቢያ አዳራሽ በሁለገብ አዳራሹ ውስጥ ተካቶ እንዲሰራ መደረጉን ገልጸዋል።

በግንባታ ላይ የሚገኘው ሁለገብ ዘመናዊ አዳራሹ ዋናውን አዳራሽ ጨምሮ የቅዱስ ሲኖዶስ መሰብሰቢያ አዳራሽ፣መጠነኛ አዳራሾች፣ቢሮዎች፣የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችን ያሟላና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎችን ለማካሔድ ምቹ የሆነ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም የማጠቃለያ ሥራዎች ላይ የሚገኝ ከቤተክርስቲያናችን ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ እንደሆነም ይታወቃል።በአሮጌው ቄራ በመገንባት ላይ የሚገኙት ሕንጻዎችም በሚጠናቀቁበት ወቅት በከተማችን የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት በመቀነስ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል።