የካቲት ፲፩ ቀን ፳፻ ፲ ወ፰ ዓ.ም
+++++++++++++++++++
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
=============
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ
ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ቤተክርስቲያን መረጃዎቿን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ማደራጀትና አገልግሎቷንም ማሳለጥ እንደሚገባት
ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ባለሙያዎችና ባለ ድርሻ አካላት ጋር ባደረጉት ውይይት ገለጹ።
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በዚሁ ጊዜ ጨምረው እንደገለጹት ቀደምት አባቶቻችን ዘመኑ በሚፈቅደው ቴክኖሎጂ ታግዘው በርካታ ውጤታማ ሥራዎችን ያከናወኑ መሆኑን ገልጸው አሁን የምንገኝ ልጆቻቸው ደግሞ ዘመኑ ያፈራውን ቴክኖሎጂ ተጠቅመን ለመጪው ትውልድ የሚሆን ሥራ መሥራት ይኖርብናል ብለዋል።
አዲሱ ትውልድ የቀደምት አባቶቹን ታሪክ ከመዘከር በተጨማሪ አቅሙን አሟጦ የራሱን አሻራ በማሳረፍ ለመጪው ትውልድ የሚሆን ሥራ መሥራት እንደሚገባው የገለጹት ብፁዕነታቸው የቤተክርስቲያናችንን ዶክሜንቶች በሙሉ ኮምፒውተራይዝድ በማድረግ ቀጣይ አገልግሎት መስጠት የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር ይገባል ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ሊቀ መዘምራን ሐረገወይን ጫኔ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይቤተክህነት ጽሕፈት ቤት የአስተዳደር መምሪያ ኃላፊ ጨምሮ በርካታ የየመምሪያው የሥራ ኃላፊዎችና ከዶክሜንቴሽን ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ሰራተኞችም ተገኝተዋል።















