መስከረም ፲፬ ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
******

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የባህር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓልን በማስመ
ልከት የእንኳን አደረሳችሁና የቅድመ ጥንቃቄ መልዕክት አስተላለፉ።

ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በዚሁ መልዕክታቸው ለመላው
ሕዝበ ክርስቲያን እንኳን ለ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ ካሉ በኋላ በዓሉ በድምቀት፣ባማረና በሰመረ መልኩ ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ ሕዝበ ክርስቲያኑ በንቃትና በሕብረት በመሆን ከጸጥታ አካላትና ቤተክርስቲያኒቱ ለዚሁ ዓላማ ካቋቋመቻቸው የኮሚቴ አባላት ጭምር በመተባበር እንዲሰራ አደራ ብለዋል።

የመንግሥት የጸጥታ ተቋማት በዓሉ ያለ አንዳች የጸጥታ ችግር ተከብሮ መዋል እንዲችል ከጠቅላይ ቤተክህነት ዐቢይ ኮሚቴ ጋር በጥምረት እየሰራ እንደሚገኝ የጠቀሱት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በበዓሉ ወቅት ለሚደረግ ፍተሻ ፍፁም ክርስቲያናዊ ትብብር እንዲያደርግ አደራ ብለዋል።የጸጥታ አስከባሪዎችም ጨዋነት በተምላና ክብርን በሚገልጽ አግባብ የፍተሻ ሥርዓቱን እንዲያከናውኑ አሳስበዋል።

ከበዓላችን መንፈሳዊ ሥርዓት ውጪ የሆኑ መልዕክቶች፣ አለባበሶች እንዲሁም የቤተክርስቲያኒቱ መገለጫ ከሆኑ ዓርማዎች ውጭ እንዳይዙ በዓሉ ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ እንደመሆኑ ቤተክርስቲያኒቱን ከማይገልጹ ሆታዎችና ጭፈራዎች እንዲርቁ በአጠቃላይ ያልተፈቀዱ ነገሮችን ሁሉ የመስቀል ደመራ በሚከበርባቸው ቦታዎች ሁሉ ይዞ መገኘት ፍጹም መንፈሳዊ የሆነውን በዓላችንን የሚያደበዝዘው ስለሆነ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

አያይዘውም ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጀ ወጣት የሰንበት ትምህርት ቤት ልጆቻችን ከሚያቀርቡት መንፈሳዊ ትርኢትና ዝማሬ ጎን ለጎን አካባቢያቸውን በመቆጣጠር በዓላችንን በሰላም እንዳናከብር የሚያደርጉ ሁኔታዎች እንዳይፈጠሩ በጥንቃቄ መጠበቅ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በሌላ መልኩም የሌሎች እምነት ተከታዮችም በነበረውና በኖረው የመከባበርና የመደማመጥ የአብሮነት ስሜት በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንዲወጡ የአደራ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የበዓሉ ዝግጅት በየደረጃው በተቋቋሙት የበዓል አዘጋጅ ኮሚቴዎች ጥረት በጥሩ ሁኔታ በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን የገለፁት ብፁዕነታቸው ከንጉሰ ነገስት አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ወዲህ ተደርጎ በማያውቅ ሁኔታ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሦስተኛ ጊዜ የመስቀል ደመራ በዓልን በድምቀት ማክበር የሚያስችል የስቴጅ፣የድምጽ ማጉያና የክብር እንግዶች ማስተናገጃ ቦታዎችን በማዘጋጀት የሚያደርገውን ተሳትፎ ያደነቁት ብፁዕ አቡነ አብርሃም የከተማ አስተዳደሩ እያደረገ ላለው ከፍተኛ አስተዋጽኦ በራሳቸውና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስ
ቲያን ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በመጨረሻም በዓሉን ስናከብር ፍቅር ሰላምንና አንድነትን እንዲሁም መግባባትን መርህ ባደረገ አግባብ መሆን አለበት ያሉት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በዓሉ ሥጋዊ ፈቃዶቻችንን የምንፈጽምበት ሳይሆን ንስሐ ያልገቡ ንስሐ የሚገቡበት የተጣሉ የሚታረቁበት የተለያዩ አንድ የሚሆኑበት የተራራቁ የሚቀራረቡበት ፍፁም የደስታና የሰላም በዓል ሆኖ እንዲከበር ማድረግ ይኖርብናል በማለት መልዕክታቸውን አጠናቀዋል።