የመጽሐፉ አዘጋጅ ነዋሪነታቸውን በሰሜን አሜሪካ ያደረጉት ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ ተፈራ ሲሆኑ ባለፈው ሳምንት ለምረቃ የበቃው አዲሱ መጽሐፋቸው “The Ethiopian Orthodox Tewahedo Church Over the Centuries: History, Worship and Doctrine” የሚል ርዕስ የያዘ ሲሆን ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ እና መሠረተ እምነት በዝርዝር የሚዳስስ በዓይነቱም በይዘቱም ለየት ያለ መጽሐፍ እንደሆነ ታውቋል።
ስለ ቤተክርስቲያን እምነትና ሥርዓት የሚናገሩ መጻሕፍት በግእዝ በስፋት የሚገኙ በአማርኛ ቋንቋ የተተረጎሙ እና በሌሎችም የሀገሪቱ ቋንቋዎች እየተጻፉ የሚገኙ ሲሆን በእንግሊዝኛ የተጻፉ ግን በጣት የሚቆጠሩ ብቻ ናቸው። ቀሲስ ዶ/ር አምሳሉ ይህንን ክፍተት ለመሙላት አስበው የተነሡ ሲሆን የመጽሐፉም ጠቀሜታ ስለኢትዮጵያ ቤ/ክ ሥርዓተ አምልኮና ዶግማ ዘመኑን በዋጀ መልኩ በእንግሊዝኛ በውጭው ዓለም ለሚገኙ በተለይ ለወጣቶች ማስተማሪያ በእጅጉ ወሳኝ መጽሐፍ መሆኑን መምህራን ተናግረዋል።
ይህ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀው የቤተክርስቲያን ታሪክና ነገረ ሃይማኖት መጽሐፍ የካቲት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. በዋሽንግተን ዲሲ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል የስብከተ ወንጌል አዳራሽ የተመረቀ ሲሆን የመረቁትም ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል፤ የዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ናቸው። ሁለት ምሁራን በመጽሐፉ ላይ የዳሰሳ ጥናት ያደረጉ ሲሆን፤ የመጽሐፉ አዘጋጅ ለሁሉም ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
በዕለቱም የዋሽንግተን እና አካባቢው ሀገረ ስብከት የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ መምህራን፣ የሰንበት ት/ቤት ዘማርያን፣ ምዕመናን እና ምዕመናት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።በአሁኑ ሰዓት መጽሐፉ በአማዞን (Amazon) ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።