……ካለፈው የቀጠለ፦

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በጠቅላይ ሥራ አስኪያጅነት ዘመነ ሢመታቸው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው በመሥራት ላይ ከሚገኙት ቀደምት ሥራዎች መካከል በከፍተኛ ጉስቁልና የሚታወቀውንና በአሮጌ መኪና መጠራቀሚያነት የሚታወሰውን የጠቅላይ ቤተክህነትን ምድረ ጊቢ ከመሰረቱ መለወጥ የሚያስችል ዕቅድ በማዘጋጀትና በቁርጠኝነት ወደ ሥራ በመግባት ምድረ ጊቢው ለዐይን ማራኪ፣ለተመለካች ውብ፣ለቤተክርስቲያን ክብር የሚመጥናና ልዕልናዋን የሚያመላክት ቅጽረ ጊቢ እንዲሆን የሚያደርግ አስደናቂ ሥራ በመሥራት እነሆ አበው የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል የሚሉት ተረት የሚገለጥበት ገራሚ ምድረ ጊቢ እንዲሆን እያደረጉት ይገኛሉ።

በሌላ በኩል የቤተክህነቱ ቅጽር (አጥር) በአሮጌ ቆርቆሮና ግንብ፣ በተጨናነቁ መጋዘኖችና በከተማ ውስጥ ጫካ የተዋጠ በአራዊትና በደረቅ ቆሻሻ የተሞላ የጠቅላይ ቤተክህነቱን ይዞታ በግልጽ የማያሳይና እጅጉን የተጨናነቀ እንዲሁም በላይ በላይ በተደረቱ የቆርቆሮ መጋዘኖችና በተጎሳቆሉ ውትፍትፍ ቤቶች የተሞላ የነበረውን ቅጽረ ጊቢ በዘመናዊ የግንብና የብረት አጥር የቤተክርስቲያን አርማ በጉልህ በሚታይበት ውብ ዲዛይን እንዲታጠር በማድረግ፣ከአገልግሎታቸው ባሻገር በተጨናነቁ አቀማመጣቸውና በተጎሳቆሉ ይዞታቸው ለአይን ምቾትን በመንሳት ጊቢውን አስፈሪና ከባድ ድባብ እንዲላበስ አድርገውት የነበሩ አሮጌና ጎስቋላ የቆርቆሮ ቤቶችና መጋዘኖችን በማንሳትም ለዕይታ ማራኪና ውብ ቅጽረ ጊቢና ምቹ የሥራ ቦታን በመፍጠር ልማትና ትክክለኛ ለውጥ ከራስና ከቤት እንደሚጀምር ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በተግባር በማሳየት ቁርጠኛ የለውጥና የልማት አባት መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በጠቅላይ ቤተክህነት ከዕቅድና ከጥናት ውጪ ከሥርጭትና ከምርት አለመጣጣም ጋር በተያያዘ በዘፈቀደ ታትመው የተከማቹ መጻሕፍትን ማከማቻነት የሚያገለግሉና በተለያዩ ጊዜያት ተደራርተው የተሰሩት የቆርቆሮ መጋዘኖች መነሳታቸውን ተከትሎ እፎይታን ያገኘው የጠቅላይ ቤተክህነቱ ቅጽረ ጊቢ ብቻ ሳይሆን ከዕቅድና ከጥናት ውጪ ታትመው የተከማቹ መጻሕፍትም ጭምር ናቸው ቀን የወጣላቸው ቢባል ፍጹም ማጋነን አይሆንም።

በቤተክርስቲያን ከፍተኛ ወጪ ታትመው በመጋዘን ተከማችተው በላይ በላይ አዳዲስ የሕትመት ውጤቶች እየተጨመሩባቸው ለዘመናት ተከማችተው የኖሩት ቅዱሳትና የታሪክ መጻሕፍትን ያሉበትን ሁኔታ ከግምት አስገብቶ መፍትሔ የሚሰጣቸው ቀርቶ ከነ መኖራቸውም አይቷቸው የማያውቅና ያያቸውም ቢኖር ከንፈር ከመምጠጥና ከአንድ ሳምንት የመገረም አጀንዳነት አልፎ ዘላቂ መፍትሔ ሰጥቷቸው የማያውቀውን እነዚህ ቅዱሳትና የታሪክ መጻሕፍትን ቀን ያወጡላቸውም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ብቻ ናቸው።

እነዚህ ለዘመናት በዘፈቀደ መንገድ የታተሙት መጻሕፍት አገልግሎት ላይ ውለው፣ ተጨማሪ ሀብትም ፈጥረው፣ አዳዲስ መጻሕፍትንም ወልደው፣የአንባቢ ፍላጎትንም አርክተው መቀጠል ሲገባቸው አለአግባብ እንዲከማቹ የተደረገውና በሌሎች መብቱ በሌላቸው አሳታሚዎች በገፍ ታትመው ገበያውን እንዲያጥለቀልቁት የተደረገውም በፕላንና በታቀደ መንገድ አንዳንድ መጻሕፍቱን ከማተም ጋር በተያያዘ ሥልጣን ተሰጥቷቸው የነበሩ የቤተክህነቱ ሹማምንት በፈጠሩት የጥቅም ሰንሰለትና በተንኮል በተደረገ ደባ እንደሆነም የታወቀ ነው።

ይህ በቤተክርስቲያን ሀብትና ንብረት ላይ የተፈጸመው ደባም እንደ ኦሮምኛ የቅዳሴ መጻሕፍትን የመሳሰሉ ታላላቅ መጻሕፍት በነዚህ ጎስቋላ መጋዘኖች ታሽገው እንዲቀመጡ፣ከገበያ እንዲጠፉና በኦሮምኛ ቅዳሴ የሚቀድሱ አካባቢዎች በፎቶ ኮፒ መጻሕፍት እንዲቀድሱ ያስገደዱ መሆናቸውም የአደባባይ ምስጢር ነው።

ታዲያ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ባደረጉት ሥር ነቀል ለውጥና ፍፁም ተቋማዊ አሰራር ዝርጋታ እነዚህ ጎስቋላ መጋዘኖች
ሸሽገዋቸው የነበሩ እንደ ኦሮምኛ ቅዳሴ መጻሕፍት አይነቶች ቅዱሳት መጻሕፍት ነጻ ወጥተው በሕጋዊ የጨረታ ሥርዓት ተሸጠው ቤተክርስቲያን ገቢ እንድታገኝ፣በፎቶ ኮፒ መጻሕፍት ለመቀደስ የተገደዱ አብያተ ክርስቲያናት የቅዳሴ መጻሕፍቱን እንደ ልብ የሚያገኙበትን ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ቤተክርስቲያናችን በገቢዋ ሌሎችና አስፈላጊ መጻሕፍን በጥናት ላይ በተመሰረተ አግባብ ማሳተም የሚያስችላትን ሥርዓትን እንዲዘረጋ ያደረገ ሲሆን ለዕይታ የሚቀፉትና ጎስቋላዎቹ መጋዘኖችም ነባር ይዞታቸውን ለዘመናዊ ልማት በመልቀቅ የብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁን የልማት ሰውነት ማሳያ ውብ ስፍራዎች ወደመሆን ለመለወጥ ተገደዋል።

እዚህ ላይ የብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁን ትዕግስት፣
ጥበ የተሞላበትን የአመራር ብቃት፣ አሳታፊነትና የባለቤትነት መንፈስ መፍጠርን ክህሎት አለማድነቅ አይቻልም።እንዴት ቢባል መላው የጠቅላይ ቤተክህነት ሠራተኛና አመራር ብፁዕነታቸውን ጨሞሮ መጻሕፍቱን በማሰባሰብና ወደ ምቹ ቦታ በማዘዋወር ሥራ ውስጥ በዘመቻ መልኩ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያደረጉበት ጥበብ አንድነት ኃይል መሆኑን፣አንድነት ፍቅርና መተባበር መሆኑን ያሳየ በመሆኑ የብፁዕነታቸውን የአመራር ጥበብ፣ ብስለትና ክህሎትን የሚያሳይ ስለሆነ ምስጋና ሊቸረው ይገባል።

ይህ የብፁዕነታቸው ተቀዳሚ ሀብትን የመታደግ፣የሀብት ብክነትን የመከለልና የተከማቹ መጻሕፍትን በአግባቡና በሕጋዊ መንገድ የማሰራጨት ሥራ ተራ የተከማቹ መጻሕፍቶችን የማሰራጨት ሥራ እግረመንገዱን ተቋምን የመታደግ፣ለቀጣይ የቤተክርስቲያን አሰራር መዘመንና መለወጥ አቅጣጫ አመላካች እንዲሆን በማድረግ ሁሉም መምሪያና ድርጅቶች አሰራራቸው የሚፈተሽበት፣
የወደፊት የአሰራር ስልታቸው በታቀደና በተደራጀ መንገድ የሚመራበት ሥርዓትን መፍጠር ይቻል ዘንድ ትልቅ የመሸጋገሪያ ድልድይ እንዲሆን ለማድረግም ጠንካራ የጥናት ኮሚቴ በቅፁዕነታቸው አመራር ሰጪነትና በጠቅላይ ቤተክህነት አስተዳደር ጉባኤ ተዋቅሮ የቤተክርስቲያናችንን መምሪያና ድርጅቶችን በመፈተሽ የለውጥ ዋዜማ ላይ እንድንገኝ ያደረጉትም እነሆ ባለ ራዕዩና ታላቁ የለውጥ አባት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ መሆናቸውን ታሪክ በወርቃማ ብዕሩ መመዝገብ ጀምሯል።
ይ ቀ ጥ ላ ል…….

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ

የካቲት 19 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ