ጥር ፲፰ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
“””””””””””””””””””””””””””
ባሕር ዳር: ኢትዮጵያ
******
በየዓመቱ በባሕር ዳር ከተማ በድምቀት የሚከበረው” የቅዱስ ጊዮርጊስ ስባር አጽሙ” ሃይማኖታዊ በዓል ዛሬም በድምቀት እየተከበረ ነው።

በበዓሉ ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያሪክ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አሥኪያጅ፣ የባሕርዳር እና የሰሜን ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ አብርሃም ተገኝተዋል። በየሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ዜጎችም በበዓሉ ላይ ታድመዋል።

ብፁዕ አቡነ አብርሃም “ሰባሩ ጊወርጊሥ ግፈኞች አጽሙን ቀጥቅጠው ቢጥሉትም በእግዚአብሔር እርዳታ እንዳይጠፋ ኾኗል” ብለዋል። የሰው ልጆችም በእምነታቸው በመጽናት ችግር እና መከራን ሁሉ በትዕግሥት ማለፍን መማር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ሁላችንም እምነታችንን በማክበር፣ ያማረ ምግባርን በመላበስ ለትውልድ መቆም አለብን ብለዋል። “ችግር እና መከራ ሁሉ ጊዜያዊ ነው፤ በእምነት በመጽናት ችግርን የምናልፍ አስተዋዮች መኾን አለብን” ሲሉም ተናግረዋል ብፁዕነታቸው።

ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጀምሮ ሌሎችም በርካታ ችግሮች በሀገሪቱ ላይ በተከሰቱ ጊዜ ሁሉ ሕዝቡ በዕምነቱ እየጸና እና እየጸለየ፤ እግዚአብሔርም እያገዘው አልፏል ብለዋል። ለወደፊቱም ፈጣሪ ሀገር እና ሕዝብን ይጠብቅ ዘንድ በመልካም ሥነ ምግባር እና በፍጹም እምነት መጸለይ እንደሚያስፈልግም ብፁዕነታቸው ተናግረዋል።

የዛሬው በዓል በድምቀት እንዲከበር ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ ተሳትፎ ለነበራቸው ወጣቶች፣ እንዲሁም ግለሰቦች እና ተቋማት ምሥጋና አቅርበዋል።

©አሚኮ