አዲስ በሚሾሙት ኤጲስቆጶሳት የአመራረጥ አካሄድ ዙሪያ በአስመራጭ ኮሚቴ አባላት ብፁዓን አባቶች ማብራሪያ ተሰጠ።
ሰኔ ፳፱ ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የግንቦት ርክበ ካህናት ምልአተ ጉባዔ ለ፯ የኦሮሚያ እና ለ፪ የደቡብ ክልል አህጉረ ስብከት በኤጲስቆጶስነት የሚሾሙ ቆሞሳትን መልምለው ለምልአተ ጉባዔ እንዲያቀርቡ የተመረጡት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ባከናወኑት የምልመላ ሂደት ዙሪያ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ተሰጥተዋል።
በተሰጠው ማብራሪያ መሠረት በእጩነት የቀረቡት ቆሞሳት በመንፈሳዊ ትምህርት፣ በአገልግሎት፣ በግብረገብነትና የሚመደቡበትን ሀገረ ስብከት ምእመናን በቋንቋቸው በማስተማር ረገድ በቂ ዝግጅት ያላቸው ስለመሆናቸው ጥቆማውን ካቀረቡት አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና ከቀረቡት ተያያዥ ሠነዶችና የሕይወት ታሪኮች መረዳት መቻላቸውንና ይህንንም ለምልአተ ጉባኤ ማቅረባቸውን በዚህም መሠረት ድምጽ ተሰጥቶ ተሿሚዎች መለየታቸውን አብራርተዋል። ምንም እንኳ ለምልአተ ጉባኤ የቀረቡት ቆሞሳት ቁጥር ፲፰ ቢሆኑም ቀድሞ በጥቆማ የቀረቡት አባቶች ቁጥር ፸፭ እንደነበሩ በኮሚቴው ጸሐፊ በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ተገልጿል።
ጥቆማው፣ ግምገማውና ምርጫው ምእመናንና ካህናት አልተሳተፉበትም በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም:- ምንም እንኳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የካህናት እና የምእመናን የጋራ የአገልግሎት ቦታ የሰማያዊት ኢየሩሳሌም አምሳል ስለመሆኗ ሁሉም የሚያምነው እውነት እንደሆነ ሁሉ ቤተክርስቲያናችን ከራሷ ልጆች ሊቃነ ጳጳሳትን መሾም ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ የምርጫ ሂደት የሚካሄደው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ብቻ በመሆኑ የዛሬውም ከቀድሞ አሠራር የተለየ አይደለም ቢሆንም ግን የካህናትንና የምእመናንን ይሁንታ ለማወቅ በተለያዩ መንገዶች ተጠቋሚዎቹ አባቶች ካገለገሉባቸው አህጉረ ስብከት እና አጥቢያዎች መረጃ ጠይቀናል ከዚህም ባሻገር ሊቃውንትንና ምእመናንን ለማሳተፍ የተሠራ ሥርዓት ሳይሠራ ወደማሳተፍ ቢገባ ችግር ሊያመጣ ይችላል የሚል ስጋት ስለመጣ በነበረው የአመራረጥ ልማድ ተከናውኗል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ጥር ፲፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም ከቀኖና ቤተክርስቲያን ውጪ ከተሾሙ አባቶች መካከል የተወሰኑት ለምን ተካተቱ በሚል ለተነሳው ጥያቄም ምላሽ የሰጡት አበው ሊቃነ ጳጳሳት አስቀድሞ የቤተክርስቲያናችንን ሰላምና መዋቅራዊ አንድነት ለመጠበቅ በተደረገው የሰላም ስምምነት መሠረት ውግዘቱ ሲነሣ ፍጹም ሰላም ስለመፈጠሩ ቅዱስ ሲኖዶስ እምነት ስላደረበት ለሲመቱ ብቁ መሆናቸው የታመነባቸው ለንስሐ የበቁ አባቶችን መግፋት አስፈላጊ ባለመሆኑ የተወሰኑት አባቶች በእጩነት ቀርበው በቅዱስ ሲኖዶስ የታመነባቸው መመረጣቸውን እንዲሁም ቀድሞ በችግሩ ወቅት በነበረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በተደረገው ውይይት በጓዳ ለመግባት የተደረገውን ሙከራ አወገዘ እንጂ በተደረገው ጥናት ያለእውቀት በተለያየ ወቅታዊ ስብከትና ጫና ተታለው የገቡ መኖራቸው በመረጋገጡ ሊመረጡ ችለዋል ሲሉ ገልጸዋል።